የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል መሠረታዊ ሠራተኛ ማህበር በ2018 በጀት ዓመት የተቋሙን ሠራተኛ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ ሥራዎችን ማከናወኑን የማህበሩ ሊቀመንበር አቶ ዳንኤል ገ/ሚካኤል ገለጹ።የሪጅን፣ የኃይል ማመንጫ፣ የዋናው መ/ቤት የዘርፍ ተወካዮች የሚሳተፉበትና ለሁለት ቀናት የሚቆየው የማህበሩ 11ኛ መደበኛ የምክር ቤት ስብሰባ በአዳማ ከተማ ተስፋዬ ኦሎምፒክ ሆቴል በዛሬው ዕለት መካሄድ ጀምሯል።
በስብሰባው ላይ የ2018 በጀት ዓመት ሪፖርትን ያቀረቡት አቶ ዳንኤል ገ/ሚካኤል የሠራተኛውን መብትና ጥቅም እንዲሁም የሙያ ደህንነትና ጤንነትን በማረጋገጥ የኢንዱስትሪ ሰላም እንዲፈጠር ከተቋሙ ማኔጅመንትና ሥራ አመራር ቦርድ ጋር ሕግና ሥርዓትን ተከትሎ በትብብር እየሰራ ነው ብለዋል።

በበጀት ዓመቱ የሕብረት ስምምነቱን መሠረት በማድረግ በደረጃ እድገት፣ በደሞዝ ስኬል ትግበራ፣ ጭማሬና ማትጊያ ክፍያ፣ የማህበሩን የገንዘብ አቅም ከማሳደግ እና ከተለያዩ ድርጅቶች ጋር በመተባበር ሠራተኛው የዱቤ አገልግሎት ተጠቃሚ ከማድረግ አኳያ አበረታች ውጤቶችን ማስመዝገቡን አስታውሰዋል።
በተጨማሪም በተቋሙ ታሪክ ያልነበሩ የቤት ኪራይ፣ የኤሌክትሪክ ማግኔክቲክ አሉታዊ ተጽዕኖ፣ የመኪና መጠበቂያ እንዲሁም የትራንስፖርት አበል ማሻሻያን ጨምሮ ሌሎች የጥቅማ ጥቅም ጥያቄዎች ምላሽ ማገኘቱንም ተናግረዋል።


የሥራ ልብስ፣ የሴፍቲ ጫማና አልባሳትን በተመለከተ በተሻለ ጥራት የሚያቀርቡ ድርጅቶችን ብቻ በማወዳደርና ግዥ ተፈጽሞ ለሠራተኛው በወቅቱ እንዲተላለፉ ከሚመለከታቸው የሥራ ክፍሎች ጋር ተቀራርቦ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
በበጀት ዓመቱ 263 አዳዲስ አባላትን ማፍራቱን የጠቆሙት አቶ ዳንኤሌ የማህበሩን የገንዘብ አቅም ለማሳደግ ባንኮችን በማወዳደር በጊዜ ገደብ ተቀማጭ በማድረግ እየሰራ መሆኑንም አብራርተዋል።
በበጀት ዓመቱ የጡረተኞች ነጻ ሕክምና ጥናት ተግባራዊ አለመደረጉ፣ የነጻ ኤሌክትሪክ ፍጆታ አለመሻሻሉን ጨምሮ ከንጹህ የመጠጥ ውኃ እና የሕጻናት ማቆያ እንዲሁም በራስ ገቢ ሠራተኛውን በተሻለ ተጠቃሚ ለማድረግ ፋይናንስ የማድረግ ውሱንነት ጋር ተያይዞ ተግዳሮቶች ማጋጠማቸውን ጠቁመዋል።
እነዚህን ችግሮች ለመፍታት የሠራተኛ ማህበሩ አዳዲስ ዕይታዎችን በመጨመር ቀጣይነት ያለው ውጤት ለማስመዝገብ የአመራር ሚናውን በማሳደግ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በአሠሪና ሠራተኛ ጉዳይ አዋጅ፣ በሕብረት ስምምነቱና በተቋሙ በሚወጡ ደንብና መመሪያዎች መሠረት በማድረግ ተቀራርቦ እንደሚሰራም አረጋግጠዋል።
ምክር ቤቱ በቆይታው ማህበሩ 2018 በጀት ዓመት ያከናወናቸው ዋና ዋና ተግባራት ሪፖርት፣ የማህበሩ የኦዲት ሪፖርት እና የማህበሩ የ2019 በጀት ዓመት ዕቅድና በጀት ላይ ውይይት በማድረግ የተለያዩ ውሳኔዎችን እንዲሁም የተሻሻሉ የሥራ መመሪያዎችን ያጸድቃል ተብሎ ይጠበቃል፡፡


💡 “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”
📌ፌስቡክ↠https://www.facebook.com/Ethioelectric
📌ቴሌግራም↠https://t.me/EEPCommuication
📌ሊንክዲን↠ https://www.linkedin.com/company/ethiopian-electric-power
📌ዩትዩብ↠https://www.youtube.com/@ethiopowermedia
📌ቲክቶክ↠https://tiktok.com/@ethio_power
📌ድረ- ገጽ ይጎብኙ https://www.eep.com.et
ሐምሌ 13 ቀን 2018 ዓ.ም