የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ከተለያዩ ተቋማት ጋር ያለውን የሥራ ግንኙነት ለማጠናከርና የአቅም ግንባታ ሥራዎችን ለማስፋፋት በያዘው ዕቅድ መሠረት ለኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ባለሙያዎች ሥልጠና መስጠት መጀመሩን አስታወቀ።
በተቋሙ የኢትዮ ፓወር አካዳሚ የሥልጠና ክፍል ተወካይ ሥራ አስኪያጅ አቶ ክብሮም ገብሬ እንደገለፁት ሥልጠናው በፓወር ላይን ሲስተም ካድ (Power Line System CAD) ሶፍትዌር እና በኃይል ማከፋፈያና የሥርጭት መስመር ዲዛይን ላይ ትኩረት ያደረገ ነው፡፡
ለአስር ቀናት በሚቆየው በዚህ ሥልጠና ባለሙያዎቹ በዘመናዊ የኮምፒውተር ፕሮግራሞች የታገዘ የኃይል ሥርጭት ቁጥጥር ስልትና በዲጂታል ቴክኖሎጂ ላይ የተመሰረቱ የዲዛይን ሥራዎችን እንዲቀስሙ ይደረጋል።



ይህም ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያዎችን እና የሥርጭት መስመሮችን ለመቆጣጠርና ዲዛይን ለመንደፍ ትልቅ እገዛ እንደሚያደርግላቸው አብራርተዋል።
እንደ አቶ ክብሮም ገለፃ ሥልጠናው በአሁኑ ወቅት በኃይል አቅርቦትና ሥርጭት ላይ የሚታዩትን ችግሮችና የአገልግሎት አሰጣጥ ጉድለቶችን በዘላቂነት ለመቅረፍ እንዲሁም የቆዩ አሰራሮችን በዲጂታል ሥርዓት ለመተካትና ለመቆጣጠር ያግዛል፡፡
ሥልጠናው በሁለቱ የኃይል አቅራቢ ተቋማት መካከል ያለውን የሥራ ትስስር ይበልጥ እንደሚያጠናክረው የገለፁት ተወካዩ ከሥልጠናው ተጨማሪ ገቢ ለማግኘትም ፋይዳው የጎላ መሆኑን ጠቅሰዋል።
በቀጣይም መሰል የአቅም ግንባታ ሥልጠናዎችን ለሌሎች ተቋማት ለመስጠት ታቅዶ እየተሠራበት እንደሚገኝም ገልፀዋል።


