የተቋሙን የፕሮጀክት አፈጻጸም የሚያሻሽሉ ሥልጠናዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ – ኢንጂነር ኤፍሬም ወ/ኪዳን

የተቋሙን የፕሮጀክት አፈጻጸም የሚያሻሽሉ ሥልጠናዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ – ኢንጂነር ኤፍሬም ወ/ኪዳን

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል በፕሮጀክት አፈጻጸምና በሌሎች ዘርፎች ላይ የሚስተዋሉ ክፍተቶችን ለመሙላት የሚያስችሉ አቅም ግንባታ ሥልጠናዎችንና የልምድ ልውውጦችን አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታወቀ፡፡

ተቋሙ ውጤታማ የፕሮጀክት አስተዳደር ሥርዓትን በመዘርጋት የማስፈጸም አቅሙን ለማሳደግ ለፕሮጀክት ዳይሬክተሮች እና ሥራ አስኪያጆች ያዘጋጀው የመጀመሪያው ዙር ሥልጠና የተቋሙ ከፍተኛ አመራሮች በተገኙበት በስኬት ተጠናቋል።

በሥልጠናው ማጠናቀቂያ መድረክ ላይ የተገኙት የተቋሙ የጀነሬሽን ቢዝነስ ዘርፍ ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ ኢንጂነር ኤፍሬም ወልደኪዳን እንደገለጹት ተቋሙ ባለፉት ሦስት አሥርት ዓመታት በርካታ የኃይል ማመንጫ፣ ማከፋፈያ ጣቢያዎች እና የማስተላለፊያ መስመር ፕሮጀክቶችን ሲያከናውን ቢቆይም ወጥ የሆነ ተቋማዊ የፕሮጀክት አስተዳደር ሥርዓት ባለመኖሩ የተገኙ ዕውቀቶች በግለሰቦች አእምሮ ውስጥ ተበታትነው ቆይተዋል።

ተቋሙ ከዚህ ቀደም ፕሮጀክቶችን ሲመራ የነበረው ዓለም አቀፍ የሙያ ማረጋገጫ (Certification) ባላቸው ባለሙያዎች ሳይሆን በቴክኒካዊ ዕውቀትና በሥራ ሂደት ውስጥ በሚቀሰም ልምድ ላይ ብቻ ተመስርቶ በመሆኑ በፕሮጀክቶች አፈጻጸም ወቅት የገንዘብ እና የጊዜ ብክነት ይስተዋል እንደነበር ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚው አስታውሰዋል።

እነዚህን ክፍተቶች ለመቅረፍ በየጊዜው የሚዘጋጁ ሥልጠናዎች በፕሮጀክቶች አፈጻጸም ወቅት የሚያጋጥሙ ማነቆዎችን በትክክል ለይቶ ለማወቅና ለቀጣይ ሥራዎች ስኬት ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳላቸው ኢንጂነር ኤፍሬም ጠቁመዋል።

በእያንዳንዱ ፕሮጀክት ውስጥ የሚገኙ ልዩ ልዩ ዕውቀቶችንና አቅሞችን በማሰባሰብም በፕሮጀክት አስተዳደር ረገድ የላቀ ብቃት ላይ መድረስ እንደሚቻል አክለዋል።

ከተጠናቀቀው የአምስት ቀናት ሥልጠና የተገኙ ተሞክሮዎችን ወደ ተግባር በመቀየር በቀጣይ በሚከናወኑ የልማት ፕሮጀክቶች ላይ አወንታዊ ተፅዕኖ ማምጣት እንደሚገባ ያሳሰቡት ኢንጂነር ኤፍሬም ወደፊት የሙያ ማረጋገጫ አሰጣጥን ከተቋሙ አሠራር ጋር ማስተሳሰር እንደሚገባ ገልጸዋል።

በፕሮጀክት አፈጻጸም ላይ የሚታዩ ችግሮች በአንድ ጀንበር የሚቀረፉ ባይሆኑም መሰል የአቅም ግንባታ ሥልጠናዎችን እና ጥናቶችን በማካሄድ ተቋሙ ከፕሮጀክት መነሻ እስከ ፍጻሜ ያለውን የማስፈጸም አቅም ማሳደግ እንደሚገባው ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚው አስገንዝበዋል።

Scroll to Top