ኢኢፒ ማስተር ተግባራዊ በመሆኑ በርካታ ውጤቶች መመዝገባቸውን ሪጅኑ ገለፀ

ኢኢፒ ማስተር ተግባራዊ በመሆኑ በርካታ ውጤቶች መመዝገባቸውን ሪጅኑ ገለፀ

በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል በሴንትራል አንድ ሪጅን በራስ ኃይል የበለፀገ ኢኢፒ ማስተር የተሰኘ ሶፍትዌር በአስር ሪጅኖች ላይ ተግባራዊ ሆኖ አበረታች ውጤት መገኘቱን የሪጅኑ ዳይሬክተር ገለፁ።

የሪጅኑ ዳይሬክተር አቶ ደረጀ ገዛኸኝ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ሠራተኛ ማህበር የስራ አስፈፃሚ ቡድን በሪጂኑ ጉብኝት ባደረገት ወቅት እንደተናገሩት ይህ የዲጂታል ሲስተም የተበታተነ እና ማኑዋል አሰራርን በማስቀረት አስተማማኝ የመረጃ አያያዝ ስርዓት እንዲሰፍን አስችሏል።

በተጨማሪም የኦፕሬሽንና የጥገና ሥራዎችን በመመዝገብ የመረጃ ተደራሽነትን ከማሳደጉ ባሻገር ለቀጣይ ስራዎች ግብአት እንደሚሆንም ዳይሬክተሩ ተናግረዋል።

ይህ የዲጂታል ሲስተም በራስ ኃይል በልፅጎ ወደ ተግባር መግባቱ ተቋሙ በሁሉም ዘርፍ አቅም ያላቸው ባለሙያዎች ባለቤት መሆኑን ያሳያል ያሉት ደግሞ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ሠራተኛ ማህበር ፕሬዚዳንት አቶ ዳንኤል ገ/ሚካኤል ናቸው።

ፕሬዚዳንቱ እንደተናገሩት ይህንን ሲስተም ያበለፀጉ ሠራተኞች በቀጣይ ሊበረታቱ እና በተቋሙ በኩል እውቅና ሊሰጣቸው ይገባል።

በትራንስሚሽን ቢዝነስ ዘርፍ የሰው ኃይል እና ንብረት አስተዳደር ዳይሬክተር አቶ ተማም አፍደል በበኩላቸው ሲስተሙ የኃይል ጭነትን፣ የኃይል መቋረጥን እና የሰው ኃይል መረጃን በዘመነ መንገድ የሚይዝ በመሆኑ ሥራን በፍጥነት እና በብቃት ለማከናዎን እንደሚያስችል ተናግረዋል።

Scroll to Top