ተቋሙ በየጊዜው የሚሰጣቸው ስልጠናዎች የተበታተኑ ዕውቀቶችን በማሰባሰብ የተሻለ ተቋማዊ ግንባታ ለማከናወን ትልቅ ፋይዳ እንዳላቸው በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የሰው ኃይል ሥራ አስፈጻሚ አቶ አታላይ አበበ ገለጹ።
ሥራ አስፈጻሚው ይህንን ያሉት ለፕሮጀክት ዳይሬክተሮች እና ሥራ አስኪያጆች በፕሮጀክት አስተዳደር ዙሪያ በተዘጋጀው ስልጠና ማስጀመሪያ መርሃ ግብር ላይ ተገኝተው ባስተላለፉት መልዕክት ነው።
አቶ ታላይ በመልዕክታቸው እንደገለጹት ስልጠናው በየፕሮጀክቶቹ ላይ የተለያየ እውቀትና ልምድ ያላቸው ባለሙያዎች ያላቸውን እውቀቶችና ልምዶች እርስ በርስ በመለዋወጥ የጋራ ግንዛቤ ለመፍጠር ከፍተኛ እገዛ ያደርጋል።
ስልጠናውን በሚገባ ተከታትለው የሚያልፉ ብቁ ባለሙያዎች እንደሚወጡ ሙሉ እምነት እንዳላቸው የገለጹት አቶ አታላይ ሰልጣኞች የሚሰጠውን ስልጠና በትኩረት እንዲከታተሉ አሳስበዋል፡፡
በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የኢትዮ-ፓወር አካዳሚ ዳይሬክተር ዶ/ር ወንዶሰን ካሳ በበኩላቸው ስልጠናው በየደረጃው የሚገኙ የፕሮጀክት ማኔጅመንት ዘርፎችን ያካተተ ሲሆን ዓለም አቀፉን የፕሮጀክት ማኔጅመንት ኢንስቲትዩት የፕሮጀክት አሰራር( የሕይወት ዑደት) የተከተለ መሆኑን ገልጸዋል።
በተቋሙ ካሉ የተለያዩ ፕሮጀክቶች ለተውጣጡ የፕሮጀክት መሪዎች የተዘጋጀው ይህ ስልጠና በተቋሙ ውስጥ ወጥ የሆኑ የፕሮጀክት መጠሪያዎችን እና አሰራሮችን በመጠቀም ተቋማዊ ቋንቋ ለመፍጠር ያለመ መሆኑን ዳይሬክተሩ ገልጸዋል፡፡
ስልጠናው ለአምስት ቀናት የሚቆየው ሲሆን የተቋሙን ነባራዊ ሁኔታ መነሻ ያደረጉ የፕሮጀክት ዕቅድ እና ትግበራ ሂደቶች፣ በፕሮጀክቶች ላይ ስለሚያጋጥሙ የሕግ ጉዳዮች እና የፕሮጀክት ውል አስተዳደርና ግዥ እንዲሁም የፕሮጀክት ክትትልና ቁጥጥር ላይ የሚያተኩር ሲሆን በተለያዩ ባለሙያዎች እንደሚቀርቡ ጠቁመዋል፡፡