የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ሠራተኛ ማህበር በ2019 በጀት ዓመት ተቋማዊ የኢንዱስትሪ ሠላም እንዲረጋገጥ የሚያስችሉ ተግባራት ላይ ከተቋሙ አመራር ጋር በቅንጅት እንደሚሰራ ገለጸ።
የማህበሩ የ2019 በጀት ዓመት ዕቅድ ለምክር ቤት አባላት በዋና ጸሐፊው አቶ ኃይሉ ወልዴ በኩል ቀርቧል።



የማህበሩ ሥራ የአንድ ጊዜ ጉዳይ (event) ሳይሆን ቀጣይነት ያለው አቅም የሚፈልግ በመሆኑ የ2019 በጀት ዓመት የማህበሩ ዕቅድ ነባራዊ ሁኔታዎችን፣ መልካም አጋጣሚዎችንና ሊያጋጥሙ የሚችሉ ተግዳሮቶችን ታሳቢ በማድረግ መዘጋጀቱን ተናግረዋል።
የኢንዱስትሪ ሠላም እንዲረጋገጥ፣ የዓመታዊ ጭማሪና የማትጊያ አበልን ጨምሮ የተጠኑ ጥቅማ ጥቅሞች በሙሉ ወቅቱን ጠብቀው ተፈጻሚ እንዲሆኑ ከተቋሙ ማኔጅመንትና የሥራ አመራር ቦርድ ጋር ተቀራርቦ እንደሚሰራ ገልጸዋል።
የዱቤና የብድር አገልግሎት ለማመቻቸት ከተለያዩ የፋይናንስ ተቋማት ጋር በቅርበት በመስራትና የሁለትዮሽ ስምምነቶችን በማጠናከር የሠራተኞችን ሕይወት የሚለውጡ ተግባራት በበጀት ዓመቱ በትኩረት እንደሚከናወኑም ተናግረዋል።
በሁሉም የሥራ ቦታዎች የሠራተኛ ክበቦች እንዲቋቋሙና ያሉትም እንዲጠናከሩ ዕቅድ መያዙን የጠቆሙት አቶ ኃይሉ የሠራተኛ የቅሬታ ምንጭ የሆኑ ጉዳዮች እንዲፈቱም ማህበሩ ትኩረት ሰጥቶ ይሰራል ብለዋል።


የአባላትን ቁጥር በማሳደግና ልዩ ልዩ የገቢ ማሳደጊያ መንገዶችን በመተግበር እና ወጭን በመቀነስ የማህበሩን የገቢ ምንጭ ለማሳደግ የሚያስችሉ አሰራሮች እንደሚዘረጉም ጠቁመዋል።
ማሀበሩ ከተቋሙ ማኔጅመንትና ሥራ አመራር ቦርድ፣ ከሥራና ክህሎት ሚኒስቴር፣ ከኃይል ማመንጫዎች እና ማዕድን ፌደሬሽን እና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በትብብር በመስራት እንዲሁም ከአቻ ማህበራት ጋር የልምድ ልውውጥ በማድረግ ቀጣይነት ያለው ለውጥ ለማስመዘገብ ርብርብ እንደሚደረግም አብራርተዋል።
በሕብረት ስምምነት ሊካተቱ በሚገቡ ጉዳዮች እና ተግባራዊ ባልተደረጉ የጥቅማ ጥቅም ጥያቄዎች ላይ የሁለትዮሽ ኮሚቴ ድርድር በቀጣይ እንደሚካሄድ የተናገሩት ዋና ጸሐፊው ሁሉም ሠራተኛ ሕግና ሥርዓትን ተከትሎ ለተቋሙ ውጤታማነት በትኩረት ሊሰራ እንደሚገባ አሳስበዋል።
በቀረበው ዕቅድ ላይ የምክር ቤት አባላት የተለያዩ ጥያቄዎችንና አስተያየቶችን አንስተው ውይይት ከተደረገ በኋላ የማህበሩ የ2019 በጀት ዓመት ዕቅድ በአንድ ድምፀ ተዐቅቦ በአብላጫ ድምጽ ጸድቋል።

