ተቋሙ ለልማት ተነሽ አርሶ አደሮች ከ5 ሚሊዮን ብር በላይ የሚያወጣ የዓይነት ድጋፍ አደረገ

ተቋሙ ለልማት ተነሽ አርሶ አደሮች ከ5 ሚሊዮን ብር በላይ የሚያወጣ የዓይነት ድጋፍ አደረገ

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ለአሰላ የንፋስ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት ግንባታ መሬታቸውን በቋሚነት ላዋሉ አርሶ አደሮች የ5 ነጥብ 18 ሚሊዮን ብር የዓይነት ድጋፍ ማድረጉን ገለፀ፡፡

በተቋሙ የጀኔሬሽን ቢዝነስ ዘርፍ የግዥ ሥራ አስኪያጅ አቶ ጀማል አህመድ እንደገለፁት አርሶ አደሮቹ ተገቢው ካሳ ተከፍሏቸው የእርሻ መሬታቸውን ለሀገራዊ ልማቱ ያዋሉ ቢሆንም ተቋሙ አርሶ አደሮችን በዘላቂነት መልሶ ለማቋቋም የወተት ላሞችን ገዝቶ ድጋፍ አድርጓል።

በዚህም ከ70 በመቶ በላይ የሚሆነው የእርሻ መሬታቸው ለፕሮጀክቱ ግንባታ ሥራ ለሰጡ 14 አርሶ አደሮች ለእያንዳንዳቸው አንድ የወተት ላም እና 3 ነጥብ 46 ኩንታል የመኖ ድጋፍ ርክክብ መደረጉን ገልፀዋል።

ተቋሙ ለድጋፉ በአጠቃላይ 5 ነጥብ 18 ሚሊዮን ብር ወጪ ማድረጉንና ከዚህ ውስጥም 4 ነጥብ 9 ሚሊዮን ብሩ ለላሞች እንዲሁም ከ281 ሺህ ብር በላይ ደግሞ ለመኖ ግዥ የወጣ መሆኑን ሥራ አስኪያጁ ጠቁመዋል።

ድጋፉ የአርሶ አደሮቹን የኑሮ ሁኔታ ከማሻሻል ባለፈ ማህበረሰቡ በተቋሙ ላይ የባለቤትነት ስሜት እንዲኖረው ለማድረግ ያለመ መሆኑን የጠቀሱት አቶ ጀማል ህብረተሰቡ በአካባቢው የሚገኙ የኤሌክትሪክ ኃይል መሰረተ ልማቶችን በባለቤትነትና በኃላፊነት ስሜት እንዲጠብቅም ጥሪ አቅርበዋል።

በአሰላ የንፋስ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት የማህበራዊ ሳይንስ ባለሙያ አቶ አዲሱ እጅጉ እንደተናገሩት ባለይዞታዎችን ለማቋቋም በተከናወነው የመልሶ ማቋቋም ምክረ-ሃሳብ ጥናት መሰረት በፕሮጀክቱ ክልል ውስጥ ካላቸው የይዞታ መሬት ከ70 በመቶ በላይ መሬታቸውን ለኤሌክትሪክ ኃይል ልማት ላዋሉ አርሶ አደሮች አንድ የወተት ላም እንዲሁም ከ50 እስከ 69 በመቶ ለልማት ላዋሉት ደግሞ የሥጋ ድልብ በሬ ድጋፍ ይደረግላቸዋል።

በዚህም በምክረ ሃሳቡ መሠረት ለ14 አርሶ አደሮች ድጋፍ መደረጉንና በቀጣይም ለሌሎች ቀሪ አርሶ አደሮች የተለያዩ የማህበራዊ ኃላፊነት ድጋፎችን ጨምሮ መሬታቸውን ለልማት ላዋሉ ለሁሉም አርሶ አደሮች የተለያዩ የግብርና ግብዓቶችና ማሽነሪዎች ድጋፍ እንደሚደረግላቸው አብራርተዋል።

የሄጦሳ ወረዳ አስተዳደር ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ንጉሴ ሆርዶፋ በበኩላቸው አርሶ አደሮችን መልሶ ለማቋቋም ተቋሙ ያከናወነው ሥራ ለሌሎች ምሳሌ የሚሆን ነው ብለዋል፡፡

ተቋሙ ያደረገው ድጋፍ የአርሶ አደሮችን ገቢ ለማሳደግና በአካባቢው ዘመናዊ የእንስሳት እርባታን ለማስፋፋት ሚናው የጎላ እንደሆነ ጠቅሰዋል፡፡

ተቋሙ ላደረገው ድጋፍ ምስጋናቸውን ያቀረቡት አቶ ንጉሴ ማህበረሰቡ የኤሌክትሪክ መሠረተ ልማቶችን በኃላፊነት ስሜት እንዲጠብቅ ለማድረግ ወረዳው በትኩረት እንደሚሰራም አረጋግጠዋል፡፡

ለአርሶ አደሮቹ የተበረከቱት ላሞች የሆሊስቲን ፍሬዥያን ዝርያ ያላቸው እንደሆኑና ላሞቹ በቀን ከ12 እስከ 20 ሊትር ወተት የመስጠት አቅም እንዳላቸው የተናገሩት ደግሞ በወረዳው የግብርናና መሬት ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ዘሪሁን መኮንን ናቸው።

ላሞቹ ለአርሶ አደሮቹ ከመሰጠታቸው በፊት የጤና ምርመራ እንደተደረገላቸው ያረጋገጡት አቶ ዘሪሁን አርሶ አደሮቹ ውጤታማ እንዲሆኑ ጽሕፈት ቤቱ ለሁለት ዓመታት አስፈላጊውን ሙያዊ ድጋፍ እንደሚያደርግም አስታውቀዋል።

ድጋፉ የተበረከተላቸው አርሶ አደሮች ይዞታቸውን ለሀገራዊ የኃይል ልማት ሲያውሉ ከተከፈላቸው ካሳ በተጨማሪ የመልሶ ማቋቋሚያ ድጋፍ ስለተደረገላቸው መደስታቸውን ገልፀው ለተደረገላቸው ድጋፍም ተቋሙን አመስግነዋል።

ድጋፉ የተበረከተላቸው አርሶ አደሮች በበኩላቸው ይዞታቸውን ለሀገራዊ የኃይል ልማት ሲያውሉ ከተከፈላቸው ካሳ በተጨማሪ የመልሶ ማቋቋሚያ ድጋፍ በመደረጉ ደስታቸውን ገልጸው ለድጋፉም ተቋሙን አመስግነዋል።

ድጋፉ የገቢ ምንጫቸውን በማሳደግ በዕለት ተዕለት የኑሮ ዘይቤያቸው ላይ ለውጥ እንደሚያመጣላቸው የተናገሩት አርሶ አደሮቹ በአካባቢው የሚገኙ የኃይል መሠረተ ልማቶችን እንደራሳቸው ንብረት በመጠበቅ ተቋሙ ያደረገላቸውን ድጋፍ እንደሚክሱም አረጋግጠዋል።

የአርሶ አደሮቹን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ሲባል ላሞቹን ከሁለት ዓመት በፊት ለሦስተኛ ወገን ማስተላለፍ እንደማይቻል በስምምነቱ ላይ መካተቱ በርክክቡ ወቅት የተገለፀ ሲሆን ለዚህም ተቋሙና የሄጦሳ ወረዳ አስተዳደር ክትትል እንደሚያደርጉ ተመላክቷል።

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ከኃይል መሠረተ ልማት ግንባታ ሥራዎች በተጨማሪ ለአካባቢው ማህበረሰብ የተለያዩ የማህበራዊ አገልግሎት ድጋፎችን እያደረገ ይገኛል።

Scroll to Top