የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል በሥሩ የሚያስተዳድራቸውን የኃይል ማመንጫዎችና የማከፋፈያ ጣቢያዎች ሕጋዊ የይዞታ ማረጋገጫ ሰነድ እንዲኖራቸው በትኩረት እየሠራ እንደሚገኝ የንብረትና ጠቅላላ አገልግሎት ሥራ አስፈጻሚ ወ/ሮ ስመኝ አያሌው አስታወቁ፡፡
ተቋሙ ካለው ከ800 ቢሊዮን ብር በላይ የሚገመት ጠቅላላ ሀብት ውስጥ የኃይል ማመንጫዎች 60 በመቶውን ድርሻ ይይዛሉ። በተጨማሪም የማስተላለፊያ መስመሮችና የማከፋፈያ ጣቢያዎች 30 በመቶ እንዲሁም በማመንጫዎችና ማከፋፈያ ጣቢያዎች የሚገኙ ሕንፃዎችና ሌሎች ንብረቶች ቀሪውን 10 በመቶ እንደሚሸፍኑ ሥራ አስፈጻሚዋ ገልጸዋል።
ከተቋሙ 25 የኃይል ማመንጫዎች ውስጥ 20 የሚሆኑት ህጋዊ የይዞታ ማረጋገጫ ካርታ እንዳላቸው የተገለፀ ሲሆን የቀሪዎቹን አምስት ማመንጫዎች ህጋዊነት ለማረጋገጥ አስፈላጊው ሂደት እየተከናወነ መሆኑ ተጠቁሟል፡፡
እንደ ወ/ሮ ስመኝ ገለጻ ተቋሙ ከሚያስተዳድራቸው የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያዎች ውስጥ 118ቱ ህጋዊ ካርታና ፕላን ያላቸው ሲሆን፤ የቀሪዎቹ 23 ጣቢያዎች የሰነድ ዝግጅት በሂደት ላይ ይገኛል፡፡
ፕሮጀክቶች ከመጀመራቸው በፊት የይዞታ ጉዳይ በግልጽ አለመቋጨቱ፣ የካሳና የመልሶ ማቋቋም ስራዎች ውስብስብነት እንዲሁም በቆዩ ጣቢያዎች ላይ የመረጃና የሰነድ እጥረት ማጋጠሙ ለይዞታ ማረጋገጫዎች መዘግየት ማነቆዎች እንደነበሩ ጠቅሰዋል፡፡
እነዚህን ተግዳሮቶች በመፍታት ሁሉም የተቋሙ ንብረቶች ህጋዊ የይዞታ ማረጋገጫ እንዲያገኙ ለማድረግ በቀጣይ ከአካባቢው ማህበረሰብና ከሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት ጋር በቅንጅት ለመስራት ትኩረት እንደሚደረግ አስረድተዋል፡፡
የተቋሙን ታሪካዊና ህጋዊ ሰነዶች በአስተማማኝ ሁኔታ ለመጠበቅ የዲጂታላይዜሽን ሥራ እየተከናወነ እንደሚገኝ የጠቆሙት ሥራ አስፈጻሚዋ በዚህም ከ1948 ዓ.ም ጀምሮ የተከማቹ በርካታ ሰነዶችን የመለየት፣ የማደራጀትና የማስወገድ ሥራ ተከናውኗል፡፡
ታሪካዊ ይዘት ያላቸው 127 ጥራዝ ሰነዶች ለኢትዮጵያ ቤተ መዛግብትና ቤተ መጻሕፍት ኤጀንሲ እንዲጠበቁ የተበረከቱ ሲሆን በአሁኑ ወቅትም የተቋሙን መረጃዎች በዘመናዊ አርካይቭ ለማደራጀት የሚያስችል የሰነድ አስተዳደር ፕሮጀክት እየተቀረጸ እንደሚገኝም ጠቁመዋል፡፡