የኃይል መሰረተ ልማት ስርቆትን ለመከላከል ከብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ጋር እየተሰራ ነው

የኃይል መሰረተ ልማት ስርቆትን ለመከላከል ከብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ጋር እየተሰራ ነው

በኤሌክትሪክ መሠረተ ልማቶች ላይ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተበራከተ የመጣውን ስርቆት ለመከላከል ከብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ጋር በቅንጅት እየሰራ መሆኑን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል አስታወቀ።

በተቋሙ የኤሌክትሪክ መሰረተ ልማት ክትትልና ቁጥጥር ቢሮ ተወካይ ሥራ አስኪያጅ አቶ ዋለ ታምሬ እንዳስታወቁት በኃይል መሠረተ ልማቶች ላይ የሚፈፀሙ ስርቆቶችን ለመከልከል ተቋሙ የተለያዩ ሥራዎችን ሲያከናውን ቆይቷል።

ይሁንና ስርቆቱ እየተስፋፋ በመምጣቱና በተቋሙ አቅም ብቻ ውጤት ማምጣት ባለመቻሉ በአሁኑ ወቅት ከብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ጋር በቅንጅት መስራት የሚያስችል አሰራር መዘርጋቱን ጠቅሰዋል፡፡

ቅንጅታዊ አሰራሩ ስርቆትን ቀድሞ ለመከላከል፣ ስርቆት የሚፈጸሙ አካላትን በመከታተል በቁጥጥር ስር ለማዋልና በተጠርጣሪዎች ላይ በህጉ መሰረት አስፈላጊውን እርምጃ ለመውሰድ የሚያግዝ መሆኑን ሥራ አስኪያጁ አመልክተዋል፡፡

አገልግሎቱ ስርቆቱ የሚያደርሰውን የጉዳት መጠን በመገንዘብ በአሁኑ ወቅት ኃላፊነት ወስዶ እየሰራ ይገኛል ያሉት አቶ ዋለ በቅርቡም ችግሩ በሚፈታበት ጉዳይ ላይ ከክልል ርዕሳነ መስተዳድሮች ጋር ውይይት ማካሄዱን አስታውሰዋል፡፡

በውይይቱ ላይ በተደረሰው መግባባት መሰረት ሁሉም ክልል የየራሱን ኃላፊነት ወስዶ ወደ ሥራ መግባቱንም ጠቁመዋል።

በስርቆት ምክንያት የኃይል መቆራረጥ እየተበራከተ በመምጣቱ ችግሩን ለመቅረፍ ተቋሙ መሠረተ ልማቱን የሚከታተልና የሚቆጣጠር የሥራ ክፍል በማዋቀር ላይ እንደሚገኝም ተናግረዋል፡፡

የሚቋቋመው የሥራ ክፍል ትኩረት የሚሹ መስመሮችን የመለየት፣ መረጃዎችን በማደራጀት ለአገልግሎቱ ሪፖርት የማድረግና የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረኮችን የማዘጋጀት ሥራዎችን እንደሚያከናውን አስረድተዋል።

እንደ አቶ ዋለ ገለፃ የሥራ ክፍሉ በሁሉም የሀገሪቱ ክፍሎች መዋቅር በመዘርጋት በየደረጃው ከሚገኙ የክልል መስተዳደር እና የጸጥታ አካላት እንዲሁም ከተቋሙ ሪጅኖች ጋር በቅንጅት ይሰራል፡፡

የስርቆት መከላከል ሥራው በሁሉም የሀገሪቱ ክፍል በሚገኙ የኃይል መሰረተ ልማቶች ላይ የሚከናወን ቢሆንም የውጪ ኃይል ትስስር እየተከናወነ ያለባቸው መስመሮችን ጨምሮ 21 ትኩረት የሚሹ መስመሮች ተለይተው ወደ ሥራ ተገብቷል፡፡

ሥራ አስኪያጁ እንዳሉት ከአገልግሎቱ ጋር መስራት ከተጀመረ ወዲህ በነሐሴ ወር ብቻ በህብረተሰቡ ጥቆማ በአዲስ አበባ የረር፣ በኦሮሚያ ባቱ እና በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ቡኢ- ቡታጂራ አካባቢዎች በስርቆት የተጠረጠሩ ግለሰቦችን በቁጥጥር ስር ማዋል ተችሏል፡፡

ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል የኤሌክትሪክ መሰረተ ልማቶችን በመጠበቅ ስርቆት የሚፈጽሙ ተጠርጣሪዎችን ለጸጥታ አካላት እንዲጠቁም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በኃይል መሰረተ ልማቶች ላይ በተፈጸመ ስርቆት በ2015 በጀት ዓመት ከ732 ሚሊዮን ብር በላይ እንዲሁም በ2016 በጀት ዓመት 817 ሚሊዮን ብር ኪሳራ መደርሱ ከዚህ በፊት መዘገባችን ይታወሳል፡፡

? “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”

Scroll to Top