በኃይል ማስተላለፊያ ምሰሶ ተሸካሚ ብረቶች ላይ የስርቆት ወንጀል ሲፈፅም የነበረ ግለሰብ እጅ ከፈንጅ ተያዘ

በኃይል ማስተላለፊያ ምሰሶ ተሸካሚ ብረቶች ላይ የስርቆት ወንጀል ሲፈፅም የነበረ ግለሰብ እጅ ከፈንጅ ተያዘ

በከፍተኛ የኤሌክትሪክ ኃይል ማስተላለፊያ ምሰሶ ተሸካሚ ብረቶች ላይ የስርቆት ወንጀል ሲፈፅም የነበረ ግለሰብ እጅ ከፈንጅ መያዙን የምስራቅ አንድ ሪጅን የኃይል ማስተላለፊያ መስመርና ማከፋፈያ ጣቢያዎች ኦፕሬሽንና ጥገና መምሪያ አስታወቀ።

በመምሪያው የኃይል ማስተላለፊያዎች የጥገና ክፍል ተወካይ ሥራ አስኪያጅ አቶ አየለ አዱላ እንደገለፁት ተጠርጣሪው 28 የኃይል ማስተላለፊያ ምሰሶ ተሸካሚ ብረቶችን ሲሰርቅ በአካባቢው የፀጥታ አካላት እጅ ከፍንጅ ተይዟል።

የስርቆት ወንጀሉ በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር መልካ ቀበሌ ልዩ ስሙ ጎላ ደን በሚባል አካባቢ በሁርሶ- አዲጋላ- ጅቡቲ የባቡር እና የኤሌክትሪክ እንዲሁም በሁርሶ- ድሬዳዋ ቁጥር-3 ባለ 230 ኪሎ ቮልት የኃይል ማስተላለፊያ ምሰሶ ተሸካሚ ብረቶች ላይ መፈፀሙን ተናግረዋል።

ሪጅኑ በሦስቱ የከፍተኛ የኤሌክትሪክ ኃይል ማስተላለፊያ መስመሮች ላይ ባደረገው የፍተሻ ሥራ 502 የምሰሶ አካላት እና 62 የምሰሶ መወጣጫ መከላከያ ብረቶች ላይ ስርቆት መፈፀሙን አቶ አየለ ጠቁመዋል።

እንደ ተወካይ ሥራ አስኪያጁ ገለፃ ከሁርሶ- አዲጋላ- ጅቡቲ ባለ 230 ኪሎ ቮልት በሚሄደው መስመር በሚገኙ 10 የኃይል ተሸካሚ ምሰሶዎች ላይ ብቻ 450 ብረቶች ለስርቆት መዳረጋቸውን አብራርተዋል።

ሪጅኑ በሚያስተዳድራቸው የኃይል ማስተላለፊያ መስመር የምሰሶ አካላት ላይ በየጊዜው ተደጋጋሚ የስርቆት ወንጀሎች እንደሚፈፀምባቸውም ነው የጠቆሙት።

መሰረተ ልማቶቹን ከስርቆት ለመታደግ በየደረጃው ከሚገኙ የዞን፣ ወረዳና የቀበሌ፣ የፀጥታና የፍትህ አካላት እንዲሁም የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር ተከታታይና ቀጣይነት ያለው የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች መሰራት እንዳለባቸው ተናግረዋል።

የመልካ ጀብዱ ፖሊስ ጣቢያ የወንጀል ምርመራ ቡድን ኃላፊ ኢንስፔክተር ዓለሙ በየነ እንደገለፁት ኑሬ ጀማል የተባለ ተጠርጣሪ በኃይል ማስተላለፊያ ምሰሶዎች ላይ በመውጣት ብረቶቹን ሲፈታ በአካባቢው በሚገኙ የፀጥታ አካላት እጅ ከፈንጅ ተይዟል።

በኃይል ምሰሶ ተሸካሚ ብረቶች ላይ ስርቆት ሲፈፅሙ ከነበሩት መካከል አንዱ ማምለጡን የገለፁት ኢንስፔክተሩ በአሁኑ ወቅት በየአካባቢው በሚገኙ የፀጥታ አካላት ጥብቅ ክትትል እየተደረገበት እንደሚገኝም ጠቅሰዋል።

የምርመራ ቡድኑ ወንጀሉን ሲፈፅም በተያዘው ተጠርጣሪ ላይ የሰነድና የሰው ምስክሮችን በማስረጃነት እያደራጀ እንደሚገኝም ጠቁመዋል።

በአካባቢው በከፍተኛ ወጪ ተገንብተው አገልግሎት እየሰጡ በሚገኙ የኤሌክትሪክ መሰረተ ልማቶች ላይ የስርቆት ወንጀል በሚፈፅሙ አካላት ላይ የሚወሰዱ እርምጃዎች ጠንካራ መሆናቸውን የገለፁት ኢንስፔክተር ዓለሙ ወንጀሎቹን ለመከላከል ሁሉም ዜጋ ኃላፊነቱን መወጣት እንዳለበትም አሳስበዋል።

? “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”

Scroll to Top