ተቋሙ ለአዲስ ዓመት በቂ ኃይል በማቅረብ የኃይል መቋረጥ እንዳይከሰት አድርጓል

ተቋሙ ለአዲስ ዓመት በቂ ኃይል በማቅረብ የኃይል መቋረጥ እንዳይከሰት አድርጓል

በ2017 አዲስ ዓመት ዋዜማ እና በዕለቱ የኤሌክትሪክ ኃይል ያለምንም እጥረት መቅረቡን በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የብሔራዊ ኃይል መቆጣጠሪያ ማዕከል አስታወቀ፡፡

ማዕከሉ እንደገለፀው በበዓሉ ዋዜማና በበዓሉ ዕለት ከ4 ሺህ 2 መቶ ሜጋ ዋት ኃይል በላይ ዝግጁ የተደረገ ቢሆንም ጥቅም ላይ የዋለው 3 ሺህ 737 ሜጋ ዋት ኃይል ብቻ ነው፡፡

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል በቂ የኤሌክትሪክ ኃይል ዝግጁ በማድረጉ በትግራይ ክልል እና በኮምቦልቻ ከሚገኙ ፋብሪካዎች በስተቀር ከፍተኛ ኃይል የሚጠቀሙ ፋብሪካዎችና ኤክስፖርት የሚደረግባቸው ሀገራት ጭምር ያለምንም የኃይል አቅርቦት ችግር እንደመደበኛው ጊዜ የኤሌክትሪክ ኃይል ማግኘታቸውንም ማዕከሉ ገልጿል፡፡

በክረምቱ ዝናብ የተነሳ የተከዜ የውሃ ኃይል ማመንጫ ግድብ የያዘውን ከፍተኛ ውሃ ለማስተንፈስ ሲባል ሥራ አቁሞ የነበረው የኃይል ማመንጫ ጣቢያው በበዓሉ ዋዜማ ሥራ እንዲጀምር በመደረጉ በትግራይ ክልል አንዳንድ ከተሞች ተከስቶ የነበረው የኃይል መቋረጥ እንዲስተካከል መደረጉንም ማዕከሉ አስታውቋል፡፡

በመላ ሀገሪቱ የሚገኙ የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያዎች እና የከፍተኛ ኃይል ማስተላለፊያ መስመሮች የኃይል መቋረጥ እንዳያጋጥም የየዘርፉ ኃላፊዎችና ሠራተኞች በዋዜማውና በበዓሉ ዕለት ተገቢውን ትኩረት ሰጥተው ሰርተዋል፡፡

? “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”

Scroll to Top