ተቋሙ የመፈጸም አቅሙን በማሳደግ ተወዳዳሪ የኃይል ማዕከል ለመሆን እየሰራ ነው

ተቋሙ የመፈጸም አቅሙን በማሳደግ ተወዳዳሪ የኃይል ማዕከል ለመሆን እየሰራ ነው

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ውስጣዊ የመፈጸም አቅሙን በማሳደግ ለሀገር ዕድገት አለኝታ የሆነና በአፍሪካ ተወዳዳሪ የኃይል ማዕከል ለመሆን እየሠራ መሆኑን አስታወቀ።

በተቋሙ የኮርፖሬት ኮሙዩኒኬሽን መምሪያ የሕዝብ ግንኙነትና ኮሙዩኒኬሽን ሥራ አስኪያጅ አቶ ፍስሐ ጌታቸው እንደገለጹት ተቋሙ አስተማማኝ ኃይል በማቅረብ ተወዳዳሪ ለመሆን የመፈጸም አቅሙን በማሳደግ ትልልቅ ፕሮጀክቶችን በራስ ኃይል እያከናወነ ይገኛል።

ቀደም ሲል በውጭ ኮንትራክተሮች ብቻ ይገነቡ የነበሩ የማከፋፈያ ጣቢያዎችና የማስተላለፊያ መስመሮች አሁን ላይ በተቋሙ የራስ አቅም እየተከናወኑ መሆኑን አቶ ፍስሐ ገልፀዋል።

እንደ ሥራ አስኪያጁ ገለጻ ተቋሙ ከ1970ዎቹ ጀምሮ በራስ ኃይል የተለያዩ የጥገና ስራዎችን ሲያከናውን የቆየ ሲሆን በአሁኑ ወቅት በግንባታ ላይ የሚገኙትን የበቆጂ፣ የገዳ ልዮ የኢኮኖሚ ዞናና የደብረታቦር ማከፋፈያ ጣቢያዎች መገንባቱ የተቋሙ ውስጣዊ አቅም ለመገንባቱ ማሳያ ነው።

የኦፕሬተር መኖሪያ ቤቶችን፣ የውስጥ ለውስጥ መንገዶች ግንባታ እና የኃይል ማመንጫ ጣቢያዎች ጥገና በተቋሙ ባለሙያዎች እየተከናወነ መሆኑን የጠቆሙት አቶ ፍስሐ በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ የተለያዩ ዘርፎች ላይ ጭምር የተቋሙ ባለሙያዎች እየተሳተፉ መሆኑን ተናግረዋል።

ይህም ተቋሙ ጊዜንና ገንዘብን በቆጠበ መልኩ ጥናቶችን መሠረት በማድረግ በተለያዩ አካባቢዎች የኤሌክትሪክ መሠረተ ልማቶችን ለማስፋፋት፣ የሕብረተሰቡን የመልማት ጥያቄዎች በዘላቂነት ለመፍታትና አስተማማኝ የኃይል አቅርቦት ለመስጠት እንዳስቻለው አብራርተዋል።

በማመንጫ፣ በማከፋፈያ ጣቢያዎችና በማስተላለፊያ መስመሮች ላይ ችግር ሲያጋጥም ከውጭ ሀገር ባለሙያ እስኪመጣ ድረስ ይከሰት የነበረውን የኃይል ብክነትና የሚወጣውን ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬን በማዳን በኩልም ሚናው የጎላ መሆኑን ገልጸዋል።

ተቋሙ የአፍሪካ የታዳሽ ኃይል ማዕከል ለመሆን የያዘውን ራዕይ ለማሳካት እና የመፈጸም አቅሙን ለማሳደግ ለሰው ኃይል ግንባታው ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑንም ጠቁመዋል።

በዚህም ከኤሌክትሮ ሜካኒካል ጋር በተያያዘ የአጭር ጊዜ ሥልጠና የሚሰጥበት የራሱ ማሰልጠኛ ተቋም እንዳለው የገለጹት አቶ ፍስሐ ከዚህ በተጨማሪም በየጊዜው የተለያዩ የሀገር ውስጥና የውጭ ስልጠናዎችን በማመቻቸት፣ ልምድ ያላቸው ሠራተኞቹን ከአዲሶቹ ጋር በማቀናጀት እና በቴክኖሎጂ የታገዙ አዳዲስ አሰራሮችን በመተግበር እየሠራ ይገኛል ብለዋል።

? “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”

Scroll to Top