የማከፋፈያ ጣቢያው ግንባታ ለበቆጂ ታሪክና የመልማት ፍላጎት ዕውቅና የሰጠ ነው

የማከፋፈያ ጣቢያው ግንባታ ለበቆጂ ታሪክና የመልማት ፍላጎት ዕውቅና የሰጠ ነው

በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የራስ ኃይል ኮንስትራክሽን መምሪያ የሚገነባው የበቆጂ ባለ230/33 ኪሎ ቮልት የማከፋፈያ ጣቢያ ለበቆጂ ታሪክና ለነዋሪዎቿ የመልማት ፍላጎት ዕውቅና የሰጠ መሆኑን የከተማው አስተዳደር ገለጸ፡፡

የከተማዋ ከንቲባ ወ/ሮ ብርሃኔ ለገሠ እንደገለጹት በቆጂ ባፈራቻቸው ብርቅዬ አትሌቶች በዓለም አደባባይ የምትታወቅ ታሪካዊ ከተማ ብትሆንም እስከአሁን ድረስ አስተማማኝ የኃይል አቅርቦት አልነበራትም፡፡

ይህም ኢንቨስተሮች ወደ አካባቢው መጥተው መዋዕለ ንዋያቸውን እንዳያፈሱና ከተማዋም በታሪኳና በመልማት አቅሟ ልክ እንዳትለማ እንቅፋት ሆኖ መቆየቱን ተናግረዋል፡፡

የአስተማማኝ የኃይል አቅርቦት የአካባቢው ሕዝብና መስተዳድር ተደጋጋሚ ጥያቄ እንደነበር የተናገሩት ከንቲባ ብርሃኔ አሁን ላይ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ጥያቄውን ለመመለስ የበቆጂ ማከፋፈያ ጣቢያን በራስ አቅም እየገነባ መሆኑን አብራርተዋል፡፡

ፕሮጀክቱ በፍጥነት እንዲጠናቀቅና አገልግሎት መስጠት እንዲጀምር ሕዝቡና መስተዳደሩ አስፈላጊውን ድጋፍና ክትትል እያደረገ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

ከማከፋፍያ ጣቢያው ግንባታ ጋር ተያይዞ አሁን ላይ ከተማዋ በልማትና ዕድገት እንድትሮጥ የሚያስችሉ በርካታ ባላሀብቶች ኢንቨስት ለማድረግ ጥያቄ እያቀረቡ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

ለአካባቢው የረጅም ጊዜ የመብራት ጥያቄ በተሰጠው ምላሽ መደሰታቸውን የሚናገሩት ከንቲባዋ በተለይም ፕሮጀክቱ በራስ አቅም በፍጥነትና በጥራት እየተከናወነ መሆኑ ልዩ ኩራት እንደፈጠረባቸው ገልጸዋል፡፡

የፕሮጀክቱ የሳይቱ አስተባባሪ አቶ እንዳልካቸው ጃምቦ በበኩላቸው የበቆጅ 230/33 ኪሎ ቮልት ማከፋፈያ ጣቢያ እና የአንድ ኪሎ ሜትር የማስተላለፊያ መስመር ግንባታ ከሚያዚያ 13 ቀን 2015 ዓ.ም ጀምሮ በራስ ኃይል እየተከናወነ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

አሁን ላይ የስዊችያርድ የሲቪልና የኤሌክትሮ ሜካኒካል ሥራው የተከላና መስመር ዝርጋታዎች እንዲሁም የቅድሚያ ፍተሻና ሙከራ ሥራ ተጠናቆ የመጨረሻውን የፍተሻና የሙከራ ሥራ ለመስራት በዝግጅት ላይ እንገኛለን ብለዋል፡፡

በፕሮጀክቱ ከሚገነቡት አራት የኃይል ማስተላለፊያ መስመር ተሸካሚ የብረት ምሰሶዎች ውስጥ የሦስት ምሰሶዎችን የመትከል ሥራ መጠናቀቁንና የቀሪው ሥራም እየተከናወነ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

እንደ አቶ እንዳልካቸው ገለጻ ከውስጥ ለውስጥ መንገድ እና ከኦፕሬተሮች መኖሪያ ቤት ግንባታ ጋር ተያይዞ የሚቀሩ ሥራዎችን በፍጥነት ለማጠናቀቅ የማካካሻ ዕቅድ አውጥተውና አስፈላጊ ዕቃዎችን አሟልተው እየሰሩ ይገኛል፡፡

በፕሮጀክቱ የሳይት ሥራ አስኪያጅ ወ/ሮ ትዕግስት በለው እንደገለጹት የፕሮጀክቱ የሲቪልም ሆነ የኤሌክትሮ ሜካኒካል ሥራ በተቋሙ የራስ ኃይል የሚከናወን ሲሆን በፕሮጀክቱ ላይ እየተሳተፉ ያሉ ሠራተኞች በሕዳሴ ግድብ ላይ ጭምር አሻራቸውን ያኖሩ ናቸው፡፡

8 ነጥብ 1 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር እና 19 ነጥብ 2 ሚሊዮን ብር በጀት ተይዞለት የሚገነባው የበቆጂ ማከፋፈያ ጣቢያና የ1 ኪሎ ሜትር ማስተላለፊያ መስመር ግንባታ ሲጠናቀቅ ለአካባቢው ከፍተኛ የኢንቨስትመንት ስበትን የሚያመጣና ኢኮኖሚውን የሚያነቃቃ ነው ብለዋል፡፡

የበቆጅ ማከፋፍያ ጣቢያ በ230 ኪሎ ቮልት ከመልካ ዋከና ተቀብሎ 10 ወጭዎች በ33 ኪሎ ቮልት ያለው ሲሆን እስከ 120 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ለሚገኙ አካባቢዎች አስተማማኝና ያልተቆራረጠ ኃይል ለማቅረብ የሚያስችል መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

? “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”

Scroll to Top