የኃይል መሰረተ ልማቱን መጠበቅ የብሔራዌ ደህንነት አጀንዳ ነው

የኃይል መሰረተ ልማቱን መጠበቅ የብሔራዌ ደህንነት አጀንዳ ነው

የኤሌክትሪክ ኃይል ግሪድ የሳይበር ጥቃት ተጋላጭ እንዳይሆን የተለያዩ የደህንነት ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑን በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የሳይበር ደህንነት መምሪያ ዳይሬክተር ገለፁ፡፡

ዳይሬክተሩ አቶ ጌትነት አድማሱ እንደተናገሩት የኤሌክትሪክ ኃይል ለሀገር ሁለንተናዊ ዕድገት የሚኖረውን አስተዋጽኦ ከግምት ውስጥ በማስገባት የኦፕሬሽናል ቴክኖሎጂውን የሳይበር ስጋት ተጋላጭ እንዳይሆን የተለያዩ ሥራዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ፡፡

የኤሌክትሪክ ኃይል መሰረተ ልማቱን ደህንነት ማስጠበቅ የብሔራዌ ደህንነት አጀንዳ በመሆኑ ተቋሙ ግሪዱን ከሳይበር ጥቃት ለመከላከል ዓለም ከደረሰበት የሚመደብ (world class) የሳይበር ደህንነት መስፈርት በማስቀመጥ እያንዳንዱ ዕቃ የደህንነት መስፈርቶችን እንዲያሟላ የሚያደርግ የአሰራር ስርዓቶችን መዘርጋቱን ገልፀዋል፡፡

አዲስ በሚገነቡ የኃይል ማመንጫዎች፣ ማከፋፈያ ጣቢያዎች እና የኃይል መቆጣጠሪያ ማዕከል ላይ የሚገጠሙ ወሳኝ ዕቃዎች እና ሲስተሞች የሳይበር ደህንነት መስፈርቶችን ባሟላ መልኩ እንዲፈፀሙ በግዥ መስፈርቶች ላይ በአስገዳጅነት ተቀምጧል ብለዋል፡፡

ተቋሙ ጀኔራል ኤሌክትሪክ (GE) ከተሰኘ የፈረንሳይ ኩባንያ ጋር በመተባበር ነባር የግሪድ ሲስተሞች እና ኔትወርኮችን ለማዘመን እና ደህንነታቸውን ለማረጋገጥ በብሔራዊ የኃይል መቆጣጠሪያ ማዕከል ፕሮጀክት እና በሁሉም የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያዎች እንቅስቃሴ መጀመሩን ዳይሬክተሩ አስታውቀዋል፡፡

ሥራው ሲጠናቀቅ ከግሪድ መሰረተ ልማት ላይ መረጃዎችን በቀላሉና በፍጥነት ለማግኘትና ለማስተላለፍ፤ በኔትወርኩ ላይ የሚያጋጥሙ ችግሮችን ለማወቅ እንዲሁም በመሰረተ ልማቱ ላይ ሊያጋጥሙ የሚችሉ የሳይበር ጥቃቶችን ለመከላከል የሚያስችሉ የሳይበር ደህንነት መከታተያና እና መቆጣጠሪያ ሲስተሞች ተግባራዊ እንደሚሆኑም ነው አቶ ጌትነት የገለጹት፡፡

ካለፉት ሦስት ዓመታት ገደማ ጀምሮ እየተከናወነ የሚገኘው  ይህ ሥራ በአሁኑ ወቅት የደህንነት ማስጠበቂያ ሲስተሞች የምርት ሂደት ላይ ፍተሻ ተከናውኖ ወደ ትግበራ ለመግባት ዝግጅት እየተደረገ ስለመሆኑም አስረድተዋል፡፡

ሲስተሞቹ ከተገጠሙ በኋላ የሳይበር ደህንነትን  ለማረጋገጥ ያላቸው ዝግጁነት ተረጋግጦ ተግባራዊ እንደሚደረጉ እና ይህም  ተቋሙን በሳይበር ደህንነት ጥበቃ ከአፍሪካ ጠንካራ የግሪድ ሲስተም እንዲኖረው እንደሚያስችለው ጠቁመዋል፡፡ 

የኦፕሬሽን ቴክኖሎጂውን ደህንነት ለማስጠበቅ በተቋሙ ታሪክ የመጀመሪያ ነው የተባለው ሥራ ተግባራዊ ሲደረግ ተቋሙ ሳምንቱን በሙሉ ለ24 ሰዓት አገልግሎት የሚሰጥ የሳይበር ደህንነት መከታተያ ማዕከል እንዲኖረው ያደርጋል፡፡

💡 “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”

Scroll to Top