በኢትዮጵያ እያደገ የመጣውን የኤሌክትሪክ ኃይል ፍላጎት ለማሟላት በመንግስት እና በግል አጋርነት የሚከናወኑ ፕሮጀክቶችን አጠናክሮ መቀጠል እንደሚያስፈልግ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል አስታወቀ።
ተቋሙ በመንግሥት እና በግል አጋርነት የሚገነቡ የኤሌክትሪክ ኃይል መሠረተ ልማቶችን ውጤታማ እንዲሆኑ የሚያግዝ የግንዛቤ ማስጨበጫ ወርክሾፕ ዛሬ በኃይሌ ግራንድ ሆቴል አካሂዷል ።
የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠናውን የሰጠው ኢንፍራጀሽን (InfraGestion) የተሰኘ የፈረንሳይ አማካሪ ድርጅት ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ጋር በመተባበር ነው።

የተቋሙ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ኢ/ር አሸብር ባልቻ በወርክሾፑ ላይ እንደተናገሩት በኢትዮጵያ እያደገ የመጣውን የኢንቨስትመንት ፍሠት ተከትሎ የደንበኞችን ፍላጎት ታሳቢ ያደረገ እና አስተማማኝ የኃይል አቅርቦት መዘርጋት ለነገ የማይባል ሥራ ነው።
ስለሆነም ተቋሙ ከሚገነባቸው የኤሌክትሪክ ኃይል መሠረተ ልማቶች በተጨማሪ የግል የኃይል አልሚዎችን በመሳብ እና በዘርፉ ላይ እንዲሰማሩ አስቻይ ሁኔታዎችን በመፍጠር የኃይል ፍላጎትን ማረጋገጥ እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል።
የሥራ ኃላፊዎች እና ባለሙያዎችም በወርክሾፑ ላይ የሚያገኙትን ግብዓት በመውሰድ በቀጣይ ለሚከናወኑ ሥራዎች እንዲጠቀሙባቸው አሳስበዋል።
በተቋሙ የኢንጅነሪንግና ኮንስትራክሽን ቢዝነስ ዘርፍ የመንግሥትና የግል አጋርነት እና የግል የኃይል አልሚዎች ፕሮጀክት መምሪያ ዳይሬክተር አቶ ተስፋዬ ጥላዬ በበኩላቸው በዘርፉ ላይ ያሉ አመራሮች እና ባለሙያዎች የግል አልሚዎችን ወደ ሀገር ማምጣት ያለው ጠቀሜታ እና የሚያግጥሙ ችግሮችን በውል መረዳት ይገባቸዋል ብለዋል፡፡
ፕሮጀክቶችን ለመገንባት ስለሚደረጉ ሂደቶች ጥልቅ ግንዛቤ በመያዝ ወደ ፊት ለሚተገበሩ ፕሮጀክቶች ንቁ ተሳታፊ እንዲሆኑ ለማስቻል ስልጠናው ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል።


በግል አልሚዎች የሚከናወኑ የኃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶች ጥብቅ ክትትል እና የጋራ መግባባት የሚጠይቁ እንዲሁም በጋራ ተጠቃሚነት መርህ ላይ የተመሠረቱ ሆነው በስኬት እንዲጠናቀቁ የተቋሙ አመራርና ባለድርሻ አካላት በጋራ መሥራት እንደሚጠበቅባቸው አስረድተዋል፡፡
በግል አልሚዎች የሚገነቡ የኃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶች ከአዋጭነት ጥናት ጀምሮ ተጠናቀው ርክክብ እስከሚፈጸም ድረስ ረጅም ጊዜ የሚወስዱ መሆኑን የጠቀሱት ዳይሬክተሩ በእያንዳንዱ ሂደት ላይ የሚያጋጥሙ ችግሮችን ተከታትሎ በጋራ መፍታት ያስፈልጋል ብለዋል።
የመንግስትና የግል አጋርነት ፕሮጀክት እንደመደበኛ የተቋሙ ሥራ የሚሰራ ሳይሆን በርካታ ባለድርሻ አካላት የሚሳተፉበት፣ ውስብስብ ሂደቶችን የሚያልፍ እና ጥንቃቄ የሚፈልግ የሥራ ዓይነት በመሆኑ የተቋሙ አመራርና ባለሙያዎች ይህን ታሳቢ ያደረገ ዝግጅት ማድረግ እንዳለባቸው አስገንዝበዋል፡፡
በሥልጠናው ላይ ተገኝተው መልዕክት ያስተላለፉት በገንዘብ ሚኒስቴር የመንግስትና የግል አጋርነት የፕሮጀክት ዝግጅት ክትትልና አቅም ግንባታ ዲቪዥን ኃላፊ አቶ ፈቃዱ ዋሚሾ በበኩላቸው በተለያዩ ዘርፎች ለማልማት ወደ ኢትዮጵያ ከመጡ 36 የግል አልሚዎች መካከል 19 የሚሆኑት በኢነርጂ ሴክተሩ ላይ መሆኑን አስታውሰዋል።
ከእነዚህ ውስጥም የአይሻ አንድ የንፋስ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት የጋራ ስምምነት ሂደቶችን አልፎ የፋይናንስ ጉዳዮች ብቻ በሂደት ላይ እንደሚገኙ የጠቆሙት ኃላፊው በቀጣይም የሌሎች የኃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶችን በመንግስትና የግል አጋርነት ማዕቀፍ ለማስጀመር እየተሰራ እንደሚገኝ አመልክተዋል፡፡
የመንግስትና የግል አጋርነት አዋጅ አልሚዎችን ለመሳብ የሚያስችሉ የህግ ማዕቀፎችን ያካተተ በመሆኑ የግል አልሚዎች ወደ ሀገር ውስጥ ሲመጡ ከአዋጭነት ጥናት ጀምሮ በእያንዳንዱ ሂደት ላይ በትኩረትና በጥንቃቄ መስራት እንደሚያስፈልግ አስረድተዋል፡፡
💡 “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”


