
የኃይል ልማት ዘርፉ ከፍተኛ ኢንቨስትመንት የሚፈልግ በመሆኑ በተቋሙ አቅም ብቻ ሊሸፈን እንደማይችል የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል አስታወቀ፡፡
ተቋሙ የ2017 በጀት ዓመት አፈፃፀም እና የ2018 በጀት ዓመት ዕቅድን አስመልክቶ ዓመታዊ ጋዜጣዊ መግለጫ በስካይ ላይት ሆቴል በሰጠበት ወቅት ከታሪፍ ማሻሽያ እና ከኃይል አቅርቦት ተደራሽነት ጋር የተያያዙ ጥያቄዎች ከመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች ተነስተዋል፡፡
ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ የሰጡት የተቋሙ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ኢንጂነር አሸብር ባልቻ ተቋሙ ከአስር ዓመታት በላይ የታሪፍ ማሻሽያ ሳያደርግ በከፍተኛ ብድር የኃይል ተደራሽነትን የሚያሳድጉ የኃይል መሰረተ ልማት ስራዎችን ሲያከናውን ቆይቷል፡፡
በዚህም ተቋሙ የህልውና አደጋ ውስጥ በመግባቱ በመንግሥት በኩል የሀገር ውስጥ ዕዳ ጫና ስረዛ እንደተደረገለት አስታውሰዋል፡፡
በተጨማሪም ተቋሙ የፋይናንስ ቁመናውን ለማሻሻል፣ የኃይል ሽፋንን ለማሳደግ እና የአገልግሎት ጥራትን ለማዘመን እንዲሁም የኦፕሬሽንና የፕሮጀክት ወጪዎችን ለመሸፈን በጥናት ላይ ተመስርቶ የታሪፍ ማሻሻያ መተግበሩን ተናግረዋል፡፡
የታሪፍ ማሻሽያው በየሩብ ዓመቱ ተከፋፍሎ በቀጣዮቹ ሦስት ዓመታት ተግባራዊ የሚደረግ መሆኑን ያስታወሱት ኢንጂነር አሸብር የታሪፍ ማሻሻያው ከጎረቤት ሀገራት አንፃር ሲታይ አሁንም እጅግ ዝቅተኛና የተቋሙን ወጪ መሸፈን የማይችል መሆኑን ገልፀዋል፡፡
በየዓመቱ የሀገሪቱ የኃይል ፍላጎት በአስር በመቶ እያደገ በመሆኑ ከታሪፍ ማሻሽያው ጎን ለጎን በዘርፉ ያለውን የኃይል ስብጥር ለማሳደግና የኤሌክትሪክ ተደራሽነትን ለማስፋት የግል አልሚዎች እንዲሳተፉ የሚያስችል የሕግ ማዕቀፍ ተዘጋጅቶ ወደ ሥራ መገባቱንም ጠቁመዋል፡፡
ይሁን እንጂ በሀገሪቱ ያለው ዝቅተኛ የኤሌክትሪክ የታሪፍ ምጣኔ የግል አልሚዎችን የሚያበረታታ ባለመሆኑ እስከ አሁን የሚፈለገው ውጤት አለመገኘቱን ገልፀዋል፡፡
የተቋሙ የትራንስሚሽን ቢዝነስ ምክትል ዋና ሥራ አስፈፃሚ ኢንጂነር አንዷለም ሲዓ በበኩላቸው በሀገሪቱ አሁን ላይ ከ40 በመቶ በላይ ለሚሆነው የህብረተሰብ ክፍል ኤሌክትሪክ ተደራሽ አለመሆኑን አንስተዋል፡፡
ያልተቆራረጠ ኃይል ለማህበረሰቡ ለማዳረስ እና የኃይል ሽፋኑን ለማሳደግ ከፍተኛ የኃይል መሰረተ ልማት ሥራዎች የሚጠይቁ በመሆናቸው የታሪፍ ማሻሻያው በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ተግባራዊ መደረጉን አንስተዋል፡፡
የታሪፍ ማሻሽያው ዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኘውን የህብረተሰብ ክፍል ታሳቢ ያደረገ ነው ያሉት ምክትል ዋና ሥራ አስፈፃሚው ጭማሪው በቀን ሲሰላ ከ55 ሳንቲም ያልበለጠ መሆኑን አብራርተዋል፡፡
የታሪፍ ማሻሽያውን አስመልክቶ የሚነሱ የተሳሳቱ አመለካከቶችን በማረም በኩል መገናኛ ብዙኃን የድርሻቸውን ሊወጡ እንደሚገባም ነው ያስረዱት፡፡
የኮርፖሬት ፋይናንስና ሀብት አስተዳደር ዘርፍ ምክትል ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ደመረ አሰፋ እንደገለፁት ተቋሙ ከዓመታዊ በጀቱ አብዛኛውን ለካፒታል ፕሮጀክቶች በመመደብ እየሰራ ይገኛል፡፡
ከአሁን ቀደም ተቋሙ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ወስዶት የነበረውና በተቋሙ የፋይናንስ ቁመና ላይ ከፍተኛ ጫና ፈጥሮ የቆየውን ብድር መንግሥት ወደ ራሱ መውሰዱን የጠቆሙት ምክትል ዋና ሥራ አስፈፃሚው ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ተቋሙ የመክፈል አቅሙንና ገቢውን ያገናዘበ ብድር ከባንኩ በመውሰድ ፕሮጀክቶችን በራሱ አቅም ለማስፈፀም እየሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡
በዚህም በ2017 በጀት ዓመት ብቻ በግንባታ ላይ ለሚገኙ ፕሮጀክቶች ማስኬጃ ከ261 ሚሊዮን ዶላር በላይ ከራስ ፋይናንስ መሸፈኑንም ተናግረዋል፡፡
በ2018 በጀት ዓመት ከያዘው 251 ቢሊየን ብር በጀት ውስጥ 71 በመቶ ለፕሮጀክቶች ማስፈፀሚያ እንደሚውል የጠቆሙት አቶ ደመረ በጀቱ ከኃይል ሽያጭ፣ ከመንግሥት ከሚገኝ ድጋፍ፣ ከአገር ውስጥና ከዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት ከሚገኝ ብድርና ድጋፍ የሚሸፈን መሆኑን አንስተዋል፡፡
💡 “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”


