የትራንፎርመር ጥገና ሥራውን እስከ ነገ ለማጠናቀቅ እየተሠራ ነው

የትራንፎርመር ጥገና ሥራውን እስከ ነገ ለማጠናቀቅ እየተሠራ ነው

በድሬዳዋ ቁጥር 3 ባለ 230/132/33/15 ኪሎ ቮልት ማከፋፈያ ጣቢያ ላይ አጋጥሞ የነበረውን የትራንስፎርመር ብልሽት እስከ ነገ አጠናቆ ወደ ሥራ ለማስገባት እየተሠራ መሆኑን የጣቢያው ሥራ አስኪያጅ አስታወቁ፡፡

ሥራ አስኪያጁ አቶ አበበው አበራ እንዳስታወቁት በቮልቴጅ አለመመጣጠን ምክንያት በጣቢያው የሚገኙ ሁለት ባለ 63 ሜጋ ቮልት አምፒር ትራንስፎርመሮች ላይ ብልሽት አጋጥሞ ነበር።

ጣቢያው ከቆቃ – ሁርሶ በ230 ኪሎ ቮልት ጥምር መስመር እና ከቆቃ – አዋሽ በ230 ኪሎ ቮልት ነጠላ መስመር እንዲሁም ከሁርሶ በ132 ኪሎ ቮልት ኃይል በመቀበል ለድሬዳዋ ከተማ፣ለድሬደዋ ቁጥር አንድ ማከፋፈያ ጣቢያ እና በዙሪያው ለሚገኙ ኢንዱስትሪዎች እንዲሁም በ132 ኪሎ ቮልት ወደ ሀረር እና አካባቢው ኃይል እንደሚሰጥ ገልጸዋል።

ይሁን እንጂ ትራንፎርመሮቹ በመበላሸታቸው ጣቢያው በ230 ኪሎ ቮልት ያገኝ የነበረው ኃይል ስለተቋረጠ በኃይል አቅርቦቱ ላይ ጫና ማሳደሩን ኃላፊው ገልጸዋል።

እንደ ኃላፊው ገለጻ መጠነኛ ጉዳት የገጠመውን አንድ ትራንስፎርመር በአስቸኳይ ጠግኖ ወደ አገልግሎት እንዲመለስ ለማድረግ ከሪጅኑና ከዋና መስሪያ ቤት የተውጣጡ ባለሙያዎች እየሰሩ ነው።

የጣቢያው የኦፕሬሽንና ጥገና ክፍል ኃላፊ አቶ ከድር አብደላ በበኩላቸው ትራንስፎርመሩ ተጠግኖ ወደ አገልግሎት ሲገባ ድሬደዋ ከተማ እና በዙሪያው ያሉ ኢንዱስትሪዎች፣ ሀረር እና አካባቢው ኃይል የሚያገኙበትን አማራጭ እንደሚያሰፋ ተናግረዋል።

ሥራ አስኪያጁ እንዳሉት ጥገናው እስከ ነገ ተጠናቆ ወደ ሥራ ሲጀምር በጣቢያው ላይ የነበረውን ጫና በከፍተኛ ደረጃ ያቃልላል።

? “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”

Scroll to Top