ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ የመጣውን የኃይል ማስተላለፊያ መስመር ተሸካሚ የብረት ምሰሶዎች ስርቆት ለመከላከል የሚያስችሉ ስልቶችን ለመተግበር መታቀዱን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ሥራ አስፈፃሚ ጽ/ቤት አስታወቀ።
በጽ/ቤቱ የአስተዳደራዊ ጉዳዮችና ዶኩመንቴሽን ቢሮ ሥራ አስኪያጅ አቶ ዋለ ታምሬ እንደገለፁት የስርቆት ተግባሩ በተቋሙ ንብረት ላይ ከፍተኛ ጉዳት ከማድረሱም ባሻገር ለኃይል መቆራረጥ ምክንያት እየሆነ መጥቷል፡፡
ተቋሙ የሚያስተዳድራቸው ከፍተኛ የኃይል ማስተላለፊያ መስመሮች በመላው ሀገሪቱ የተዘረጉ በመሆናቸው ከክልል ርዕሰ መስተዳደሮች ጀምሮ እስከ ቀበሌ አመራሮች የሚደርስ ቋሚ የግንኙነት እና የውይይት መድረኮች ለመፍጠር እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡
የኃይል ማስተላለፊያ መስመር ተሸካሚ የብረት ምሰሶዎች ስርቆት በተደጋጋሚ በሚከሰትባቸው አካባቢዎች ከሚገኙ የአስተዳደር አካላት እና የማህበረሰብ ክፍሎች ጋር በመሆን ችግሩን ከመሰረቱ ለማመፍታት የሚያስችሉ ሥራዎች እንደሚሰሩም ነው ያስታወቁት፡፡
እንደ አቶ ዋለ ገለፃ ከአስተዳደራዊ ሥራዎች ባሻገር ችግር በዘላቂነት ለመፍታት በቴክኖሎጂ የተደገፉ የተለያዩ አሰራሮችን ለመተግበር ታቅዷል፡፡
ከእነዚህ መካከል የታወር ስርቆትን ለመከላከል የሚያግዙ የታወር መቃኛ ሴንሰር (Tower Surviellance System) እና የኤሌክትሪክ ትራንስሚሽን መከታተያ ሴንሰር ተግባራዊ ለማድረግ መታቀዱን ጠቁመዋል፡፡
የፊዚካል ሴኪዩሪቲ አቅምን ለማጎልበት የሚያስችሉ የአደረጃጀት እና የማዘመን ሥራዎች እንደሚከናወኑም ገልፀዋል፡፡
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል በ2015 ዓ.ም ብቻ በኤሌክትሪክ መሠረተ-ልማት ሥርቆት ከ100 ሚሊየን ብር በላይ ኪሳራ እንዳጋጠመው መዘገባችን ይታወሳል።
? “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”

