በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል በተገባደደው በጀት ዓመት ከግዢ ሂደት፣ ከፕሮጀክት አመራር፣ ከጥቅም ግጭት እና ከካሳ ክፍያ አፈፀፀም ጋር የተያያዙ አስራ ስድስት ጥቆማዎች መቅረባቸውን በተቋሙ የሥነ-ምግባርና ፀረ-ሙስና መከታተያ ሥራ አስፈጻሚ አስታወቁ፡፡
ሥራ አስፈጻሚው አቶ መርጋ ተረፈ እንደገለጹት ከቀረቡት ጥቆማዎች መካከል በአስራ አራቱ ላይ አስፈላጊው የማጣራት ሥራ ተከናውኖ ለሚመለከተው አካል የውሳኔ ሀሳብ ቀርቧል፡፡
የተቀሩት ሁለቱ ጥቆማዎችም በማጣራት ሂደት ላይ እንደሚገኙ ሥራ አስፈፃሚው ገልጸዋል፡፡
የአሰራር ሥርዓቶች ግልጽና ተጠያቂነት ያለባቸው እንዲሆኑ ለማድረግና የሕግ ተገዥነት ለማሳደግ በበጀት ዓመቱ ከ1 ሺህ 6 መቶ በላይ ለሚሆኑ የተቋሙ ሠራተኞችና የሥራ መሪዎች በሥነ-ምግባር ግንባታ ላይ ያተኮሩ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠናዎች መሰጠታቸውንም ተናግረዋል፡፡
የተሰጡት የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠናዎች የተቋሙ የሥራ መሪዎችና ሠራተኞችን የአገልጋይነት አመለካከት እንዲያዳብሩ፣ ከአድሎና ሙሰኝነት የፀዱ እንዲሆኑ፣ የመንግስት ሀብትና ንብረትን በአግባቡ እንዲጠቀሙ በማድረግ ተቋሙ የተጣለበትን ሀገራዊ ተልዕኮ በብቃት ለመወጣት የሚያስችሉ ናቸው ብለዋል፡፡
የሥራ ክፍሉ የሚቀርቡለትን ጥቆማዎችና ቅሬታዎች ከማጣራትና ድንገተኛ ፍተሻ ከማድረግ ጎን ለጎን ሠራተኞችና የሥራ መሪዎች ወደ ዲሲፕሊን ችግሮች እንዳይገቡ የሚከላከል የሥነ-ምግባር መመሪያ መሰራጨቱንም ገልፀዋል፡፡
እንደ ሥራ አስፈፃሚው ገለፃ በበጀት ዓመቱ ሀብታቸውን እንዲያስመዘግቡ በህግ ግዴታ ከተጣለባቸው ኃላፊዎች በተጨማሪ ለሙስና ተጋላጭ የሆኑ 210 ሠራተኞችም ሀብታቸውን እንዲያስመዘግቡ ተደርጓል፡፡
? “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”