የታሪፍ ክለሳው የኃይል ዘርፉ ላይ መሰረታዊ ለውጥ ለማምጣት አስፈላጊ ነው

የታሪፍ ክለሳው የኃይል ዘርፉ ላይ መሰረታዊ ለውጥ ለማምጣት አስፈላጊ ነው

የታሪፍ ክለሳው በኃይል ልማት ዘርፉ ላይ መሰረታዊ ለውጥ ለማምጣት አስፈላጊ መሆኑን የታሪፍ ክለሳ የጥናት ቡድን ገለጸ።

የጥናት ቡድኑ አባልና የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የፋይናንስ አስተዳደር ዳይሬክተር አቶ አለማየሁ መንግስቱ የታሪፍ ክለሳው ያስፈለገበትን ምክንያት የሚዳስስ የጥናት ጽሁፍ አቅርበዋል።

በጥናት ጽሁፉ ላይ እንደተጠቀሰው የኃይል ሽፋኑንና የተቋማቶቹን የፋይናንስ ቁመና ለማሻሻል፣ በማስተላለፊያና ማሰራጫ መስመሮች ላይ ያለውን ብክነት ለመቀነስ፣ የኃይል ፍላጎትን ለማሟላት፣ የአገልግሎቱን ጥራት ለማዘመን እና የኃይል ኤክስፖርቱን በማሳደግ ዘርፉን ለመደጎም የታሪፍ ማሻሻያው አስፈላጊ ነው።

በሀገሪቱ አሁን ላይ የኤሌክትሪክ አገልግሎት ተደራሽነት 55 በመቶ መሆኑን የገለፁት አቶ ዓለማየሁ ሽፋኑን ወደ 74 በመቶ ለማሳደግ የታሪፍ ማሻሻያው ወሳኝ መሆኑን ጠቁመዋል።

እንደ አቶ አለማየሁ ገለጻ በሥራ ላይ ያለው ታሪፍ ለተቋሙ ገቢ ማደግ ድርሻ ቢኖረውም የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ላለፉት 6 ዓመታት በአማካይ በየዓመቱ ለ26 ቢሊዮን ብር ኪሳራ ሲዳረግ ቆይቷል ብለዋል።

እንደ አቶ ዓለማየሁ ገለፃ ተቋሙ እንደ አዲስ ከተቋቋመበት ከ2006 ዓ.ም ጀምሮ 177 ቢሊዮን ብር ጠቅላላ ኪሳራ አጋጥሞታል።

በሀገሪቱ ከፍተኛ የኃይል ተጠቃሚ ኢንዱስትሪዎች ፍላጎት አሁን ካለበት ከ3 ሺ 271 ጊጋ ዋት ስዓት ወደ 5 ሺ 205 ጊጋ ዋት ስዓት ለማሳደግና የመካከለኛና ዝቅተኛ ኃይል ተጠቃሚ ኢንዱስትሪዎችን የኃይል ፍላጎት ደግሞ ከ739 ጊጋ ዋት ሰዓት ወደ 3 ሺ 260 ጊጋ ዋት ስዓት ለማሳደግ ከፍተኛ ፋይናንስ እንደሚፈልግ ጠቁመዋል።

የታሪፍ ማሻሻያው የኃይል መቆራረጥ ድግግሞሹን በከፍተኛ ደረጃ በመቀነስ በሀገሪቱ ያለውን የኃይል ፍላጎት ጥያቄ አስተማማኝ በሆነ መልኩ በመፍታት የኢንዱስትሪዎችን የማምረት አቅም ለማሳደግ ከፍተኛ ሚና እንደሚኖረው አብራርተዋል።

በማስተላለፊያ መስመሮች ላይ ያለውን ብክነት አሁን ካለበት ከ7 በመቶ ወደ 5 በመቶ እንዲሁም በማሰራጫ መስመሮች ላይ ያለውን ብክነት ከ18 በመቶ ወደ 12 በመቶ በመቀነስ በአገልግሎት ዘርፍ የሚታዩ የአገልግሎት ችግሮችን ለመቅረፍ የታሪፍ ማሻሻያው አስፈላጊ መሆኑም አብራርተዋል።

የኃይል ኢንቨስትመንቱን በማሳደግ በአሁኑ ወቅት ለውጪ ሀገራት የሚቀርበውን አንድ ሺ 665 ጊጋ ዋት ስዓት የኃይል መጠን በአማካኝ በየዓመቱ 22 በመቶ ለመጨመር ታቅዶ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።

ይህም ከሀገር ውስጥ ደንበኞች የሚጠበቀውን ተሰብሳቢ ዓመታዊ ገቢ ዝቅ በማድረግ የሀገር ውስጥ ደንበኞችን ታሪፍ ለመደጎም የሚያስችል ነው ብለዋል።

አሁን በሥራ ላይ ያለው ታሪፍ በሀገር ውስጥና በውጭ አገራት ባለው የዋጋ ንረት ምክንያት አቅሙ ከ35 በመቶ በላይ መቀነሱን የገለጹት አቶ አለማየሁ የታሪፍ ክለሳው የኃይል ኢንቨስትመንቱን ለማሳደግ ይረዳል ነው ያሉት።

? “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”

Scroll to Top