የታሪፍ ማሻሻያ ባለመደረጉ ተቋሙ ለኦፕሬሽንና የጥገና ሥራዎች በየዓመቱ በአማካይ 26 ቢሊየን ብር ኪሳራ እያስተናገደ ነው

የታሪፍ ማሻሻያ ባለመደረጉ ተቋሙ ለኦፕሬሽንና የጥገና ሥራዎች በየዓመቱ በአማካይ 26 ቢሊየን ብር ኪሳራ እያስተናገደ ነው

በ2011 ዓ.ም የተተገበረው ታሪፍ ላይ ማሻሻያ ባለመደረጉ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ለኦፕሬሽንና የጥገና ሥራዎች በየዓመቱ በአማካይ 26 ቢሊየን ብር ኪሳራ እያስተናገደ መሆኑን የተቋማቱ የታሪፍ ክለሳ የጥናት ቡድን አስታወቀ።

የጥናት ቡድኑ አባልና የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የፋይናንስ አስተዳደር ዳይሬክተር አቶ ዓለማየሁ መንግስቱ እንደገለፁት በሥራ ላይ ባለው ታሪፍ ሁለቱ የኃይል አቅራቢ ተቋማት የኦፕሬሽንና የተወሰኑ የፕሮጀክት ወጪዎችን በመጠኑ መሸፈን ችለዋል።

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የታሪፍ ማሻሻያ ከተደረገ በኋላ ከ6 ነጥብ 3 ቢሊየን ብር ተነስቶ በየዓመቱ በአማካይ የ5 ቢሊየን ብር ዕድገት እያሳየ በአሁኑ ወቅት ወደ 29 ቢሊየን ብር መድረሱን አቶ አለማየሁ ተናግረዋል።

እንደ ጥናት ቡድኑ አባል ገለፃ ተቋሙ ባለፉት አራት ዓመታት ከሰበሰበው ገቢ ውስጥ በየዓመቱ አማካይ የ5 ቢሊየን ብር ገቢ ዕድገት እያሳየ ነው።

ይሁንና በሚያከናውናቸው የፕሮጀክት ግንባታ፣ የኦፕሬሽንና የጥገና ሥራዎች በየዓመቱ በአማካይ 26 ቢሊየን ብር ኪሳራ እያስተናገደ መሆኑን ጠቅሰዋል።

የታሪፍ ማሻሻያው መተግበር ከጀመረ ወዲህ 1 ሺህ 347 ከተሞችን በኤሌክትሪክ ተደራሽ ማድረግ እንደተቻለ የጠቆሙት አቶ ዓለማየሁ የኃይል ተጠቃሚ ደንበኞች ቁጥር በ1 ነጥብ 8 ሚሊየን ጭማሪ ማሳየቱን ተናግረዋል።

ባለፉት አራት ዓመታት በአገልግሎት አሰጣጥና የአከፋፈል ሒደቶች ላይ ይነሱ የነበሩ ቅሬታዎችን ለመፍታት የዲጂታላይዜሽን ሥራዎች መጀመራቸውን አመልክተዋል።

ይሁን እንጂ ላለፉት 6 ዓመታት በሥራ ላይ የቆየው ታሪፍ የኃይል አቅራቢ ተቋማቱ በፋይናንስ እንዲጠናከሩና የአገልግሎት አሰጣጣቸውን እንዲያሻሽሉ እገዛ ቢያደርግም የሚፈለገውን ለውጥ ማምጣት እንዳልቻለ ነው አቶ ዓለማየሁ የገለፁት።

በአሁኑ ወቅት በትግበራ ላይ ያለው የኃይል ሽያጭ ታሪፍ ዓለም ከደረሰበት የኢኮኖሚ ዕድገት ጋር ተመጣጣኝ ባለመሆኑ በኃይል አቅራቢ ተቋማቱ የፋይናንስ ቁመና ላይ ከፍተኛ ጫና ማሳደሩን አብራርተዋል።

በቀጣይ ተቋማቱ የተሻለ አገልግሎት ለመስጠትና ተደራሽነታቸውን ለማሰፋት የታሪፍ ክለሳ ተዘጋጅቶ ለአስተያየት መቅረቡን የጥናት ቡድኑ አባል ተናግረዋል።

? “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”

Scroll to Top