የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል እና የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ባዘጋጁት የታሪፍ ክለሳ ምክረ ሀሳብ ዙሪያ ከባለድርሻ አካላት ጋር በአድዋ ሙዚየም የስብሰብ አዳራሽ እየመከሩ ነው።
በውይይቱ ላይ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የነዳጅና ኢነርጂ ባለሥልጣን የዋና ዳይሬክተር ተወካይ አቶ በላይነህ ግዛው አሁን በሥራ ላይ ያለው ታሪፍ ላለፉት አስራ ሁለት ዓመታት ለውጥ ያልተደረገበት በመሆኑ የኃይል አቅራቢ ተቋማቱን ለኪሳራ መዳረጉን ገልጸዋል።
በሀገሪቱ እያደገ የመጣውን የኃይል ፍላጎት ጥያቄ ለማሟላትና የተሻለ የኤሌክትሪክ ኃይል በማቅረብ የአገልግሎት ተደራሽነቱን ለማስፋት የሚያስችል የኤሌክትሪክ ታሪፍ መዘጋጀቱን ተናግረዋል።
የታሪፍ ማሻሻያው አስተማማኝ የኤሌክትሪክ ኃይል ለማቅረብ፤ የጥገና ሥራዎችን ለማከናወን፣ የኃይል አማራጮችን ለማስፋት እንዲሁም የኃይል ኤክስፖርት ዘርፉን በማሳደግ የመሰረተ ልማት ማስፋፋት ስራውን የሚያግዝ መሆኑን ጠቁመዋል።
የውይይት መድረኩ ዓላማ በተዘጋጀው የታሪፍ ማሻሻያ ጥናት ዙሪያ ከባለድርሻ አካላት የሚሰጡ አስተያየቶችን ለማሰባሰብና ግልጽነት ለመፍጠር መሆኑን አቶ በላይነህ ተናግረዋል።
የታሪፍ ማሻሻያው በሚቀጥሉት ሳምንታት ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ይቀርባል ተብሎ ይጠበቃል።
? “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”





