የታሪፍ ክለሳ ጥናቱ ዝቅተኛ የኤሌክትሪክ ኃይል የሚጠቀሙ የህብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ የሚያደርግ መሆኑን የሁለቱ የኃይል አቅራቢ ተቋማት ዋና ሥራ አስፈፃሚዎች አስታወቁ።
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ሥራ፧ አስፈፃሚ ኢንጂነር አሸብር ባልቻ እንደተናገሩት ኢትዮጵያ በኤሌክትሪክ አቅርቦት ተደራሽነት ዝቅተኛ አፈፃፀም ካላቸው ሀገራት ተርታ የምትሰለፍ ናት።
ተቋሙ የኃይል አቅርቦቱን በስፋት ተደራሽ ለማድረግ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ የሚያስፈልጋቸውን ግብዓቶች እንደሚጠቀም ነው የተናገሩት።
ባለፉት ዓመታት በሥራ ላይ የቆየው ታሪፍ የኃይል አቅራቢ ተቋማቱ በፋይናንስ እንዲጠናከሩና የአገልግሎት አሰጣጥ ደረጃቸውን እንዲያሳድጉ እገዛ ቢያደርግም የሚፈለገውን እንዳላመጣ ዋና ሥራ አስፈፃሚው ገልፀዋል።
እንደ ኢንጅነር አሸብር ገለፃ የውጭ ምንዛሪ በየጊዜው እያሳየ ያለው ዕድገት በኃይል ማመንጫ፣ ማስተላለፊያና ማከፋፈያ ጣቢያ ግንባታዎች ላይ አሉታዊ ጫና አሳድሯል።
ሁለቱ የኃይል አቅራቢ ተቋማት የኤሌክትሪክ ሽፋንን እና የአገልግሎት አሰጣጥ ጥራትን ለማሳደግ ለሚያከናውኗቸው ተግባራት የታሪፍ ማሻሻያው አስፈላጊ እንደሆነም ነው አፅዕኖት የሰጡት።
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ሽፈራው ተሊላ በበኩላቸው በሀገር አቀፍ ደረጃ የህብረተሰቡን የኃይል ፍላጎት ጥያቄ ለማሟላት ከ26 ቢሊየን ብር በላይ ፋይናንስ የሚጠይቁ ፕሮጀክቶች እየተከናወኑ ነው።
ተቋሙ እየተስተዋሉ የሚገኙ የኃይል መቆራረጦችን ለመቅረፍም የመሰረተ ልማት ማዘመን፣ የደንበኞች አገልግሎት አሰጣጥ፣ የውስጥ አቅምን እና የፋይናንስ ቁመናን የማሳደግ ሥራዎች እያከናወነ እንደሚገኝም ነው ዋና ሥራ አስፈፃሚው የጠቆሙት።
የአዲስ አበባን የኤሌክትሪክ ኔትወርክ ለማሻሻል እየተከናወነ የሚገኘው ፕሮጀክት ሦስተኛው ደረጃ ላይ መድረሱን አቶ ሽፈራው አመልክተዋል።
እንደ ዋና ሥራ አስፈፃሚው ገለፃ ተቋሙ የአገልግሎት አሰጣጥ ተደራሽነቱን አጠናክሮ መቀጠል እንዲያስችለው የታሪፍ ክለሳው ተግባራዊ መደረግ አለበት።
የታሪፍ ማሻሻያው የህብረተሰቡን የመክፈል አቅም ያገናዘበና የአገልግሎት አሰጣጡን የሚያሳድግ እንደሆነም ነው ያብራሩት።
የነዳጅ እና ኢነርጂ ባለስልጣን የኢነርጂ ዘርፍ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ አህመድ ሰኢድ እንደገለፁት የታሪፍ ማሻሻያው በየአራት ዓመቱ መከለስ የሚገባው ቢሆንም ሳይሻሻል በመቆየቱ በኃይል አቅራቢ ተቋማቱ ላይ ከፍተኛ ችግር ፈጥሯል።
በባለሥልጣኑ በመመሪያ ቁጥር 008/2014 መሠረት የታሪፍ ክለሳ ሲደረግ ኃይል አቅራቢ ተቋማቱ የኦፕሬሽን ወጪያቸውን እንዲሸፍኑ የሚያደርግ ታሪፍ መዘጋጀት እንዳለበት እንደሚደነግግም ተናግረዋል።
የኃይል አቅራቢ ተቋማቱ በፋይናንስ እና በአሰራር ጠንካራ ሆነው የኤሌክትሪክ ተደራሽነትን ለማስፋት እንዲችሉ የታሪፍ ክለሳው ተገቢና ወቅቱን የጠበቀ መሆን እንዳለበት ነው አቶ አህመድ የገለፁት።
የምክክር መድረኩ ዛሬም ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች እና ባለድርሻ አካላት ጋር ይቀጥላል።
“ከካርቦን ልቀት የፀዳ አስተማማኝ የኤሌክትሪክ ኃይል!”




