የተቋሙ ፕሮጀክት የኢትዮጵያ ተቋማት የስኬት ሽልማት ተሸላሚ ሆነ

የተቋሙ ፕሮጀክት የኢትዮጵያ ተቋማት የስኬት ሽልማት ተሸላሚ ሆነ

በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የታላቁ ኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ፕሮጀክት የኢትዮጵያ ተቋማት የስኬት ሽልማት ተሸላሚ ሆነ፡፡

በአድዋ ድል መታሰቢያ ሙዚየም በተካሄደ የስኬት ሽልማት ሥነ ስርዓት ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ(ዶ/ር) የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ፕሮጀክትን ጨምሮ ለአምስት ተቋማት ሽልማት አበርክተዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ሽልማቱን ባበረከቱበት ወቅት እንደተናገሩት ተቋማቱ በሀገር ብቻ ሳይሆን በአህጉር ደረጃ ባላቸው የመወዳደር አቅምና ባስገኙት ውጤት ተሸላሚ ሆነዋል፡፡

በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ፕሮጀክት በአፍሪካ አንደኛ ብቻ ሳይሆን በአፍሪካ ከፍተኛ ፈተና የገጠመው እንደሆነ ጠቁመው ፕሮጀክቱ ፈተናውን ተቋቁሞ የኢትዮጵያዊያንን ቁጭትና የመልማት ፍላጎት እያሳካ ይገኛል ብለዋል፡፡

በፕሮጀክቱ ብዙ ያልተነገሩ ታሪኮችና ምስጢሮችን በውስጡ ስለያዘና በአፍሪካ የመጀመሪያው ስለሆነ ተሸላሚ እንዳደረገው ተናግረዋል፡፡

እንደ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገለፃ ፕሮጀክቱ ቀደም ሲል በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ቢያልፍም ባለፉት ዓመታት ችግሮችን ለመፍታት በተሰጠው አመራር ውጤታማ ሆኗል፡፡

ሽልማቱን የተቀበሉት በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የታላቁ ኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ፕሮጀክት ሥራ አስኪያጅ ኢንጂነር ክፍሌ ሆሮ በበኩላቸው የላቁ ተቋማትን መሸለም ለተሻለ ሥራ ራሳቸውን እንዲያዘጋጁ ከማድረጉም ባለፈ በቀጣይ ለሌሎች መነሳሳትን የሚፈጥር ነው፡፡

ዕውቅናው በፕሮጀክቱ ግንባታ ሥራ ላይ በተሰማሩት ስም የተበረከተ ቢሆንም ፕሮጀክቱን ለስኬት ላበቁት ለሁሉም ኢትዮጵያዊያን የተሰጠ ነው ብለዋል፡፡

ሽልማቱ ፕሮጀክቱን በትጋት በማጠናቀቅ የኢትዮጵያዊያን ተስፋ የሆነውን ግድብ ዕውን ለማድረግና በቀጣይ የተሻለ ሥራ ለማከናወን እንደሚያነሳሳም ጠቁመዋል፡፡

ከታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ፕሮጀክት በተጨማሪ የግብርና ሚኒስቴር፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ ኢትዮ ቴሌኮም እና የኢትዮጵያ ፖስታ አገልግሎት የኢትዮጵያ ተቋማት የስኬት ሽልማት ተሸላሚ ሆነዋል፡፡

Scroll to Top