የአሸጎዳ ባለ 230/33 ኪሎ ቮልት የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያ የማስፋፊያ ግንባታ አፈፃፀም 34 በመቶ መድረሱን የፕሮጀክቱ ሥራ አስኪያጅ አስታወቁ።
ሥራ አስኪያጁ አቶ አብርሃም አባተ እንዳስታወቁት በኃይል ማከፋፈያ ጣቢያው እየተከናወነ የሚገኘው የማስፋፊያ ግንባታ የሲቪል ሥራ 30 ነጥብ 1 በመቶ እንዲሁም የኤሌክትሮሜካኒካል ሥራ 4 በመቶ ተጠናቋል።
የኃይል ማስፋፊያ ሥራውን በተያዘው በጀት ዓመት አጠናቆ ለአገልግሎት ዝግጁ ለማድረግ እየተሰራ እንደሚገኝ ነው የገለፁት።
የሁለት ባዝባር ማስፋፊያ፣ የውስጥ ለውስጥ መንገዶች፣ የአጥር ሥራ፣ የፍሳሽ ውሃ ማስወገጃ ግንባታዎች በፕሮጀክቱ ከሚከናወኑ ዋና ዋና ሥራዎች መካከል እንደሚጠቀሱ ተናግረዋል።
40 ሜጋ ቮልት አምፒር አቅም ያላቸው ሁለት ትራንስፎርመሮችን የማስቀመጥ ሥራ መከናወኑን የገለፁት አቶ አብርሃም ትራንፎርመሮቹ 64 ሜጋ ዋት ኃይል የመጫን አቅም እንዳላቸውም ገልፀዋል።
እንደ አቶ አብርሃም ገለፃ የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያ የማስፋፊያ ግንባታው ሰባት ባለ 33 ኪሎ ቮልት ወጪ መስመሮች አሉት።
የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያው የማስፋፊያ ሥራ ሲጠናቀቅ 70 ካሬ ለሚባለው የመቐለ ከተማ አዲስ መንደር፣ ለኢታካ ጨርቃጨርቅ ፋብሪካ፣ ለአዲጉዶም፣ ለሔዋኔ ከተማና አካባቢው እንዲሁም ወደፊት ለሚገነቡ የኢንዱስትሪ መንደሮች አስተማማኝ የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት ተደራሽ ለማድረግ ሚናው የጎላ መሆኑን ገልፀዋል።
የማስፋፊያ ፕሮጀክቱን በ8 ወራት ጊዜ አጠናቆ ለአገልግሎት ለማብቃት ከ219 ነጥብ 9 ሚሊዮን ብር በላይ በጀት መያዙንም ነው የጠቀሱት።
የአሸጎዳ የማከፋፈያ ጣቢያ የማስፋፊያ ፕሮጀክት ግንባታን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የራስ ኃይል መምሪያ እያከናወነው ሲሆን ፓወር ቻይና የተሰኘ ኩባንያ በዕቃ አቅርቦት እየተሳተፈ ይገኛል።
“ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”


