የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል እና የኢትዮ- ኢንጂነሪንግ ግሩፕ በጋራ መስራት በሚችሉባቸው ጉዳዮች ላይ የሁለትዮሽ ውይይት አካሂደዋል።
ውይይቱ በኢ.ፌ.ዴ.ሪ የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ይዞታና አስተዳደር አስተባባሪነት ሁለቱ ተቋማት በቅንጅት መስራትና ልምዶችን መለዋወጥ እንዲችሉ ለማድረግ ያለመ ነው።
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ሥራ አስፈፃሚ ኢንጂነር አሸብር ባልቻ በውይይቱ ወቅት እንደተናገሩት የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ ለማሳደግ የውስጥ አቅምን በማጠናከርና ያሏትን ሃብቶች አሟጦ መጠቀም ይገባል።
በአሁኑ ወቅት ኢትዮ-ኢንጂነሪንግ ግሩፕ በአዲስ ራዕይና አመራር የተቋቋመ ተቋም በመሆኑ የመደገፍና ውጤታማ የሚሆንበትን ሁኔታ በማመቻቸት በጋራ ለመስራት ተቋማቸው ዝግጁ መሆኑን አረጋግጠዋል።
የሁለቱ ተቋማት በትብብር መስራት የውጭ ምንዛሪ እጥረትን ለማስወገድ፣ የሥራ ዕድሎችን ለመፍጠርና ከውጭ ጥገኝነት ለመላቀቅ እንዲሁም የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ ለማነቃቃት ሚናው የጎላ መሆኑንም ነው ኢንጂነር አሸብር የገለፁት።
በቀጣይም ተቋሙ ከኢትዮ-ኢንጂነሪንግ ግሩፕ የጥራት ደረጃቸውን ያሟሉ የኤሌክትሪክ ግብዓቶችን በጥናትና በዕቅድ ለይቶ ለመግዛት እንዲያስችለው የቴክኒክ ቡድን በማዋቀር ወደ ሥራ እንደሚገባ ዋና ሥራ አስፈፃሚው ጠቁመዋል።
የኢትዮ- ኢንጂነሪንግ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አምባሳደር ሱሌማን ደደፎ በበኩላቸው ተቋማቸው ትልቅ ራዕይ ይዞ እየተንቀሳቀሰ የሚገኝ ቢሆንም ከሌሎች መንግሥታዊ ተቋማት ጋር በትብብር ካልሰራ ውጤታማ ሊሆን አይችልም።
ሁለቱ ተቋማት የሚያጋጥማቸውን የውጭ ምንዛሪ እጥረት ችግር ለመቅረፍ በጋራ መስራት እንደሚጠበቅባቸው አምባሳደር ሱሌማን ተናግረዋል።
ተቋሙ ወደፊት ኢትዮጵያ ውስጥ ከሚያከናውናቸው የልማት ሥራዎች ባሻገር ከጎረቤት ሀገራት ጋር በትብብር ለመስራት ማቀዱንም ነው ዋና ሥራ አስፈፃሚው የገለፁት።
በኢ.ፌ.ዲ.ሪ የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ይዞታና አስተዳደር የማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ሥራ አስፈፃሚ አቶ ገረመው ቀኖ እንደተናገሩት የሁለቱ ተቋማት ትብብር ተጠናክሮ እንዲቀጥል አመራሩ ቁርጠኛ ሊሆን ይገባል።
አስተዳደሩ በተቋማት መካከል የሚፈጠሩ ቅንጅታዊ አሰራሮች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ ለማድረግ የተለያዩ ድጋፎችን እንደሚያከናውንም ነው አቶ ገረመው ያመለከቱት።
በውይይቱ ላይ ሁለቱ ተቋማት የቀድሞ የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ብረታ-ብረት እና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን ወይም ሜቴክ ከተቋሙ ጋር ለነበረው ሥራ ወደ ሀገር ውስጥ ባስገባቸው ብረታ-ብረቶች፣ ማሽነሪዎች እና ተሽከርካሪዎች የወደፊት ዕጣ ፈንታ ላይም መክረዋል።
በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ውስጥ በሚገኙ የባለቤትነት ማረጋገጫ ሰነድ የሌላቸው ተሽከርካሪዎች ላይ ያሉ ችግሮችን ለመቅረፍ የኢ.ፌ.ዴ.ሪ የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ይዞታና አስተዳደር እገዛ እንዲያደርግ ኢንጂነር አሸብር ጠይቀዋል።
“ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”


