የተቋሙ የሥራ መሪዎች በአንድ ጀምበር የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ላይ ተሳተፉ

የተቋሙ የሥራ መሪዎች በአንድ ጀምበር የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ላይ ተሳተፉ

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የሥራ መሪዎች”በመትከል ማንሰራራት” በሚል መሪ ቃል በሀገር አቀፍ ደረጃ በአንድ ጀምበር 7 መቶ ሚሊየን ችግኞችን ለመትከል እየተካሄደ ባለው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ላይ ተሳትፈዋል።

የተቋሙ የሥራ መሪዎችና ሠራተኞች ባለፉት ዓመታት በተከናውኑ የአረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብሮች ላይ በንቃት ሲሳተፉ የቆዩ ሲሆን በዛሬው ዕለትም በተለያዩ የተቋሙ ሥራ ቦታዎች ላይ አሻራቸውን አሳርፈዋል።

በቢሾፍቱ ቁጥር 3 ማከፋፈያ ጣቢያ በተካሄደው የችግኝ ተካላ ላይ የተሳተፉት በተቋሙ የኢትዮ ፓወር አካዳሚ ዳይሬክተር ወንድወሰን ካሳ (ዶ/ር) እንደገለፁት የተቋሙ አመራርና ሠራተኞች ንቅናቄው ከተጀመረ ጊዜ ጀምሮ ባለፉት ዓመታት በተለያዩ አካባቢዎች ችግኞችን በመትከል ሀገራዊ ኃላፊነታቸውን ሲወጡ ቆይተዋል።

በዛሬው ዕለት በተቋሙ የተካሄደው የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር እንደ ሀገር የተያዘውን ዕቅድ ከማሳካት ባለፈ ተቋሙ ከአረንጓዴ ኢኮኖሚ ስትራቴጂ የተቀዳ  የታዳሽ ኃይል አማራጮችን ለመጠቀም  እየሰራ ላለው ሥራ አጋዥ ስለመሆኑም ጠቁመዋል።

የተቋሙ ከፍተኛ አመራሮች በመርሃ ግብሩ ላይ መሳተፋቸው ለሠራተኛው አርአያ ይሆናል ያሉት ዳይሬክተሩ የተቋሙ የሥራ መሪዎችና ሠራተኞች በታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ ላይ እንዳደረጉት ርብርብ ሁሉ በአረንጓዴ አሻራ ላይ የመሪነት ሚና በመያዝ ማስቀጠል እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

በተቋሙ የጀኔሬሽን ቢዝነስ ዘርፍ የቴክኒካል ድጋፍ መምሪያ ዳይሬክተር አቶ ዮናስ ተስፋዬ በበኩላቸው የአረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብሩ በሀገሪቱ የሚገኙ የኃይል ማመንጫ ግድቦችን ከጎርፍና ከደለል በመከላከል ለረጅም ዓመት እንዲያገለግሉ ያደርጋል ብለዋል።

ከዚህ በተጨማሪም የአካባቢ ስነ- ምህዳርን በማመዛዘን ወደ ግድቦች በቂ የውሃ ፍሰት እንድኖር በማድረግ ማመንጫ ጣቢያዎች የሚጠበቅባቸውን የኤሌክትሪክ ኃይል እንዲያመርቱ ለማድረግ ሚናው የጎላ መሆኑንም ተናግረዋል።

በተቋሙ የኮርፖሬት ኮሙዩኒኬሽን መምሪያ ዳይሬክተር አቶ ሞገስ መኮንን እንደተናገሩት የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብሩ የውሃ አካላት እንዲያገግሙ በማድረግ ግድቦች የውሃ እጥረት እንዳይገጥማቸው ያግዛል።

ከዚህ በፊት እንደ ሀገር የተከናወኑ የችግኝ  ተከላ ሥራዎች በግድቦች የውሀ አያያዝ ላይ ለውጥ ማምጣቱን በማስታወስ ይህም የተቋሙ ማመንጨት አቅም ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ እንዲሄድ አስችሏል ብለዋል።

እንደ አቶ ሞገስ ገለፃ የአረንጓዴ አሻራው ሥነ ምህዳርን በመጠበቅ የተቋሙን የሥራ ቦታዎች ለኑሮ ምቹ  ከማድረግ ባለፈ የምግብ ዋስትናዋን በማረጋገጥ በኩል የራሱን አስተዋፅዖ እያበረከተ ይገኛል።

በመርሃ ግብሩ ላይ የተሳተፉት የሴቶች ህፃናትና ማህበራዊ ጉዳዮች መምሪያ ዳይሬክተር ወ/ሮ ሌንሴ ኢደኤ እና የፀረ ሙስናና ሥነ ምግባር መምሪያ ዳይሬክተር አቶ ደረጀ አጥናፌ በሀገራዊ ንቅናቄው ላይ መሳተፋቸው እንዳስደሰታቸው ገልፀው መርሃ ግብሩ ለቀጣይ ትውልድ ፅዱና አረንጓዴ ኢትዮጵያን ለማስተላለፍ ይረዳል ብለዋል።

የቢሾፍቱ ቁጥር 3 ማከፋፈያ ጣቢያ ሥራ አስኪያጅ አቶ ሲሳይ አይቸው በበኩላቸው በጣቢያው ከዚህ በፊት ምንም አይነት ችግኝ እንዳልነበረ አንስተዋል።

ከዚህ በፊት በተከናወኑ ተመሳሳይ መርሃ ግብሮች ከ1ሺህ በላይ ችግኞችን በመትከል የግቢውን የአየር ንብረት መቀየር የተቻለ ሲሆን በዛሬው ዕለትም ለምግብነት የሚውሉ ችግኞች መተከላቸውን ገልፀዋል።

መርሀ ግብሩ ለተቋሙ የሚኖረውን ሚና በመረዳት ሠራተኛውና አመራሩ ለስኬቱ የድርሻውን እንዲወጣ እና ችግኞቹን ከመትከል ባለፈ በመንከባከብ ላይ ትኩረት ሰጥቶ መሰራት እንዳለበት የሥራ ኃላፊዎቹ አሳስበዋል። 

በዕለቱ በዋና መስሪያ ቤቱ የሚገኙ ከፍተኛ የሥራ መሪዎች በሞጆ፣ ቦሌ ለሚና ቢሾፍቱ ማከፋፈያ ጣቢያዎች ላይ ካከሄዱት የችግኝ ተከላ ሥራ በተጨማሪ በኃይል ማመንጫዎች፣ በሌሎች ማከፋፈያ ጣቢያዎች እና በሪጅን ቢሮዎች እየተከናወነ ይገኛል።

? “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”

Scroll to Top