መርሀ ግብሩ ተቋሙ የአፍሪካ የታዳሽ ኃይል ማዕከል ለመሆን የያዘውን ዕቅድ ለማሳካት ሚናው የጎላ ነው – ኢንጅነር አሸብር ባልቻ

መርሀ ግብሩ ተቋሙ የአፍሪካ የታዳሽ ኃይል ማዕከል ለመሆን የያዘውን ዕቅድ ለማሳካት ሚናው የጎላ ነው – ኢንጅነር አሸብር ባልቻ

የአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር በሀገር አቀፍ ደረጃ ለ7ኛ ጊዜ “በመትከል ማንሰራራት” በሚል መሪ ቃል በአንድ ጀንበር በ294 ሺ ሄክታር መሬት ላይ 700 ሚሊዮን ችግኞችን የመትከል መርሀ ግብር በዛሬው ዕለት እየተከናወነ ይገኛል።

‎የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ሥራ አስፈጻሚ ኢንጅነር አሸብር ባልቻን ጨምሮ የተቋሙ የሥራ መሪዎች፣ የማዕከላዊ ሁለት ሪጅንና የጣቢያው ሠራተኞች በሞጆ ቁጥር ሁለት ማከፋፈያ ጣቢያ የችግኝ ተከላ አከናውነዋል።

‎በመርሀ ግብሩ ላይ የተቋሙ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ኢንጅነር አሸብር ባልቻ እንደገለጹት የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ሠራተኞችና የሥራ መሪዎች ባለፉት ጊዜያት በተካሄዱ የአረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብሮች በንቃት ሲሳተፉ ቆይተዋል፡፡

‎በየዓመቱ የሚካሄደው የአረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብር ተቋሙ አረንጓዴ እና ጽዱ ኢትዮጵያን በመፍጠር የታዳሽ ኃይል አማራጮችን በመጠቀም የኤሌክትሪክ ኃይል በማመንጨት እና በማስተላለፍ የአፍሪካ የታዳሽ ኃይል ማዕከል ለመሆን የያዘውን ዕቅድ ለማሳካት ጉልህ አበርክቶ እንዳለው ገልጸዋል።

‎የኃይል ማመንጫ ግድቦችን ከደለል በመከላከል የግድቦችን ደህንነት ለማስጠበቅ እንደሚያስችል የጠቆሙት ዋና ሥራ አስፈጻሚው ወቅቱን የጠበቀ ዝናብ እንዲኖር በማድረግ አስተማማኝ ኃይል ለማመንጨት የሚረዳ ነው።

‎ተቋሙ በማመንጫና ማከፋፈያ ጣቢያዎች በአረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብሩ ትኩረት ሰጥቶ እየተከላቸው የሚገኙ ችግኞች ለምግብነት የሚውሉ መሆኑንም አንስተዋል።

‎በመሆኑም በአረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብሩ ላይ ሁሉም ሠራተኛ በንቃት በመሳተፍ ለሀገራዊ ጥሪው በጎ ምላሽ እንዲሰጥ አሳስበዋል።

‎የችግኝ ተከላው ላይ የተሳተፉ የሥራ መሪዎችና ሠራተኞች በበኩላቸው የአረንጓዴ አሻራ ፕሮግራሙ ጽዱና አረንጓዴ አካባቢን በመፍጠር የምግብ ዋስትናዋን ያረጋገጠች ሀገር ለትውልድ ለማስተላለፍ ከፍተኛ ሚና አለው ብለዋል።

‎መርኃ ግብሩ የተራቆቱ አካባቢዎችን በደን ለመሸፈንና በምግብ ራስን ለመቻል ጉልህ ሚና ያለው መሆኑን በመረዳት ችግኞቹን ከመትከል ባለፈ በመንከባከብም ሁሉም ኃላፊነቱን ሊወጣ እንደሚገባ ገልጸዋል።

‎በተመሳሳይ የተቋሙ የሥራ መሪዎችና ሠራተኞች ከሞጆ ቁጥር ሁለት ማከፋፈያ ጣቢያ በተጨማሪ በቦሌ ለሚ፣ በቢሾፍቱ ቁጥር ሦስት እና በሁሉም የኃይል ማመንጫ እና ማከፋፈያ ጣቢያዎች የአረንጓዴ አሻራቸውን አሳርፈዋል።

? “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”

Scroll to Top