የማከፋፈያ ጣቢያው ለከተሞች መስፋፋትና የኢኮኖሚ ዕድገት ሚናው የጎላ ነው

የማከፋፈያ ጣቢያው ለከተሞች መስፋፋትና የኢኮኖሚ ዕድገት ሚናው የጎላ ነው

የራይቱ ማከፋፈያ ጣቢያ በአካባቢው ለሚገኙ ከተሞች መስፋፋትና ለኢኮኖሚ እድገት ከፍተኛ ሚና እየተወጣ መሆኑን በኦሮሚያ ክልል ምሥራቅ ባሌ ዞን የራይቱ ወረዳ አስተዳደር አስታወቀ፡፡

የወረዳው አስተዳደር ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ተሾመ ጉታ እንዳስታወቁት ማከፋፈያ ጣቢያው አገልግሎት መስጠት ከመጀመሩ በፊት ወረዳው ከምሽቱ 12 ሰዓት እስከ ሌሊት 6 ሰዓት ብቻ በነዳጅ መብራት ሲያገኝ ነበር፡፡

በዚህ የተነሳ በአካባቢው የተለያዩ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች በስፋት ይስተዋሉ እንደነበር አንስተዋል፡፡

የማከፋፈያ ጣቢያው መገንባት ለወረዳዉ ማህበረሰብ የኤሌክትሪክ ኃይል ከማቅረብ ባለፈ የተለያዩ በረከቶችን ይዞ መምጣቱንም አቶ ተሾመ ገልፀዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት የወረዳው መቀመጫ ደደቼ በላ ከተማን ጨምሮ በወረዳው ሥር የሚገኙ ስድስት ቀበሌዎች ከማከፋፈያ ጣቢያው አስተማማኝ የኤሌክትሪክ ኃይል በማግኘታቸው ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች እየተቃለሉ  መምጣታቸውን ተናግረዋል፡፡

እንደ ኃላፊው ገለጻ የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦቱ በወረዳው ኢንቨስትመንትን በመሳብ፤ የተለያዩ መሰረተ ልማቶች እንዲስፋፉ እና የአካባቢው ወጣቶች በተለያዩ የሥራ ዘርፎች እንዲሰማሩ በማስቻል ለከተሞች መስፋፋትና ለአካባቢው ኢኮኖሚያዊ እድገት ከፍተኛ ሚና መጫወቱን አስረድተዋል፡፡

በተጨማሪም የአካባቢው ማህበረሰብ ዘመናዊ የአኗኗር ዘይቤ እንዲከተል እና የተለያዩ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም የመረጃ ባለቤት እንዲሆን ማስቻሉን ጠቅሰዋል፡፡

የደደቼ በላ ከተማ ከንቲባ አቶ አወል ኡመር በበኩላቸው የማከፋፈያ ጣቢያው በከተማዋ ላይ መገንባቱ የነዋሪዎች ተጠቃሚነት እንዲረጋገጥ በማድረግ የከተማዋ ወጣቶችን በብረታ ብረት፣ በእንጨት ሥራዎችና በጎሚስታ አገልግሎቶች እንዲሰማሩ በማድረግ የሥራ ዕድል ፈጠራን እያገዘ ስለመሆኑ አብራርተዋል፡፡

ለማህበረሰቡ ኢኮኖሚያዊ እድገት እያደረገ ካለው አስተዋጽዖ ባለፈ ከአካባቢው አየር ፀባይ ጋር በተያያዘ የሚደርሱ ማህበራዊ ችግሮችን በማቃለል የራሱን ሚና እየተወጣ ይገኛል ብለዋል፡፡

ማህበረሰቡ የኤሌክትሪክ ኃይልን ሚና በመገንዘብ መሰረተ ልማቶችን በኃላፊነት እንዲጠብቅ  ከግንዛቤ ማስጨበጫ ጀምሮ የተለያዩ ሥራዎችን ለማከናወን አስተዳደራቸው ቁርጠኛ መሆኑንም የሥራ ኃላፊዎቹ አረጋግጠዋል፡፡

? “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”

Scroll to Top