የተቋሙ የህጻናት ማቆያና መንከባከቢያ ማዕከል እውቅና ተሰጠው

የተቋሙ የህጻናት ማቆያና መንከባከቢያ ማዕከል እውቅና ተሰጠው

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ለሴት ሠራተኞቹ ምቹ የሥራ አካባቢ ለመፍጠር ያቋቋመው የህጻናት ማቆያና መንከባከቢያ ማዕከል “የሞዴል ማዕከል” እውቅና ማግኘቱን በተቋሙ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳዮች መምሪያ አስታወቁ፡፡

የመምሪያው ዳይሬክተር ወ/ሮ ሌንሴ ኢደኤ እንዳስታወቁት የህጻናት ማቆያና መንከባከቢያ ማዕከሉ በሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር እውቅና ከተሰጣቸው ሰባት ሞዴል የህጻናት ማቆያና መንከባከቢያ ማዕከላት መካከል ግንባር ቀደም ሆኗል፡፡

የማዕከሉ ከባቢያዊ ሁኔታ፣ የህጻናት መመገቢያ፣ መኝታና፣ መጫወቻ ክፍሎች ስፋት፣ የመጸዳጃና የመታጠቢያ ክፍሎች ሁኔታ እና የህጻናት ቅበላ መስፈርት እንዲሁም የሞግዚትና የህጻናት ንጽጽር ተቋማቱ የተወዳደሩባቸው መስፈርቶች እንደነበሩ ተናግረዋል፡፡

ማዕከሉ በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የተቀመጡ የጥራት መስፈርቶችን አሟልቶ በመገኘቱ፣ ምቹ የሥራ ከባቢ በመፍጠሩ እና የተሻለ አፈጻጸም በማስመዝገቡ የእውቅና የምስርክ ወረቀትና 50 ሺህ ብር የሚገመት የቁሳቁስ ሽልማት እንደተበረከተለት ወ/ሮ ሌንሴ ገልጸዋል፡፡

የተገኘው እውቅና በቀጣይ ለሚሰሩ ሥራዎች ትልቅ ተነሳሽነትን የሚፈጥር መሆኑን የገለጹት ዳይሬክተሯ ይህ ውጤት እንዲመዘገብ እገዛ ላደረጉ የተቋሙ ከፍተኛ ማኔጅመንትና የተለያዩ ባለድርሻ አካላት ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡ 

በዕለቱ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይልን ጨምሮ የኢንፎርሜሽን መረብና ደህንነት አገልግሎት፣ የምዕራብ አዲስ አበባ ግብር ከፋይ ቅ/ጽ/ቤት፣ የከፍተኛ ግብር ከፋዮች ቅ/ጽ/ቤት እና ገቢዎች ሚኒስቴር እውቅና ከተሰጣቸው ተቋማት መካከል ይገኙበታል።

Scroll to Top