የተቋሙን የግዥ ሥርዓት ለማዘመን እየተሰራ ነው

የተቋሙን የግዥ ሥርዓት ለማዘመን እየተሰራ ነው

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የግዢ ሂደቶቹን ለማዘመን ፔራጎ ኢንፎርሜሽን ሲስተምስ ከተሰኘ ሀገር በቀል ኩባንያ ጋር ሥራ ሊጀምር ነው፡፡

የግዢ ሥርዓት ማዘመኛ ፕሮጀክት ትግበራውን ለማስጀመር በተዘጋጀው የውይይት መድረክ ላይ የተቋሙ እና የኩባንያው የሥራ ኃላፊዎችና ባለሙያዎች ተሳትፈዋል፡፡
 በፕሮጀክቱ የማስጀመሪያ መድረክ ላይ ንግግር ያደረጉት የተቋሙ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ሙላት ገዛኸኝ እንደገለፁት በተቋሙ የሚከናወኑ የተለያዩ ሥራዎች በወረቀት አልባ መንገድ እንዲመሩ ለማድረግ ትኩረት ተሰጥቶት እየተሰራ ይገኛል።

ተቋሙ ግዢዎቹን ጨምሮ ሌሎች ሥራዎቹን በዲጂታል ሥርዓት ታግዞ ማከናወኑ በአሰራር ላይ ለሚያጋጥሙ ችግሮች በቀላሉ መፍትሔ ለመስጠት እና ሥራዎቹን ለማቀላጠፍ እንደሚያስችል አንስተዋል።

በተቋሙ የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ዘርፍ ሥራ አስፈፃሚ ወ/ሮ ጽዮን በቀለ በበኩላቸው ተቋሙ በተያዘው በጀት ዓመት የተለያዩ አሰራሮቹን ከማኑዋል ወደ ዲጅታል ሥርዓት መቀየሩን ገልፀዋል፡፡



የተቋሙን የግዥ የአሰራር ሥርዓት ለማዘመን ፔራጎ ኢንፎርሜሽን ሲስተምስ ከተሰኘ ሀገር በቀል ኩባንያ ጋር ስምምነት በማድረግ ወደ ሥራ መገባቱንም አስታውቀዋል፡፡

ከኩባንያው ጋር የተደረገው ስምምነት ሲስተሙ ወደ ሥራ ሲገባ ድጋፍ የሚያደርግበትን ጊዜ ጨምሮ የ21 ወራት የትግበራ ጊዜ እንዳለው አንስተዋል።

የፔራጎ ኢንፎርሜሽን ሲስተምስ ኩባንያ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ እውነቱ አበራ እንደተናገሩት  ውይይቱ ፕሮጀክቱ ወደ ትግበራ መግባቱን እና ባለድርሻ አካላት የሚኖራቸውን ሚና ለማስተዋወቅ  ያለመ ነው፡፡

 የሲስተም ማልማቱ ሥራ በተቋሙ አሁን ያለውን የግዥ አሰራር የመለየት፣ ሲስተሙን ተቋሙ ከሚፈልገው አሰራር ጋር እንዲሄድ የማድረግና ከሌሎች ሲስተሞችና አሰራሮች ጋር እንዲናበብ የማድረግ፤ የስልጠናና አቅም ግንባታ እንዲሁም ሲስተሙን ወደ ትግበራ የማስገባትና የድጋፍና ጥገና ሥራዎችን እንደሚያጠቃልል አስረድተዋል፡፡

ሲስተሙ የግዥ ሥርዓቱን ግልጽነትንና ተጠያቂነትን በሚያስፈን፣ ከሌሎች የተቋሙ ሲስተሞች እና ከግዥ ህጎችና ደንቦች ጋር በተናበበ፣ ባለደረርሻ አካካት በቀላሉ በሚረዱትና እምነት በሚጥሉበት መልኩ ተዘጋጅቶ እና የሳይበር ደህንነት ፍተሻ ተደርጎበት ወደ ትግበራ  እንደሚገባ አስታውቀዋል፡፡

ኩባንያው በኢትዮጵያና በሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ባከናወነው ሥራ ያገኘውን ልምድ ተጠቅሞ ፕሮጀክቱን ውጤታማ ለማድረግ በትኩረት እንደሚሰራ አረጋግጠዋል፡፡

በውይይቱ  ላይ በመገኘት  የቀጣይ አቅጣጫ የሰጡት በተቋሙ የፋይናንስና ሀብት አስተዳደር ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ደመረ አሰፋ ሲስተሙ በግዥ ሂደት ግልጽነትንና ተጠያቂነትን ለማስፈን፣ ግዥዎቹን በወቅቱ ለመፈፀም እንዲሁም በሦስተኛ ወገን የሚጠየቁ መረጃዎችን በወቅቱ ለማቅረብ እንደሚያስችል  ተናግረዋል፡፡



ኩባንያው የተቋሙን አሰራር ለማዘመን ላሳየው ፍላጎት አመስግነዋል፡፡

በመድረኩ ከፕሮጀክቱ ትግበራ ጋር የተያያዙ ጥያቄዎችና አስተያየቶች ተነስተው በኩባንያው ዋና ሥራ አስፈጻሚ በአቶ እውነቱ አበራ ምላሽና ማብራሪያ ተሰጥቶባቸዋል፡፡

Scroll to Top