የተቋሙን የሥራ አፈፃፀም መለኪያ መስኮች ለማሻሻል ይሰራል

የተቋሙን የሥራ አፈፃፀም መለኪያ መስኮች ለማሻሻል ይሰራል

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የሚያከናውናቸውን የኃይል መሠረተ ልማቶች ግንባታና የኦፕሬሽን ሥራዎች እንዲሁም አስተዳደራዊ ጉዳዮች የሥራ አፈፃፀም መለኪያዎችን ለማሻሻል እንደሚሰራ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ አስታወቀ።

የተቋሙን የ6 ወራት አፈፃፀም ሪፖርት ለኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ  ያቀረቡት የኮርፖሬት ፕላኒንግ ዘርፍ  ሥራ አስፈፃሚ አቶ ህይወት እሸቱ ተቋሙ በፕሮጀክት ግንባታ፣ በኦፕሬሽን፣ በፋይናንስ፣ በለውጥ ሥራዎች እንዲሁም በሰው ኃይል አስተዳደርና አቅም ግንባታ ሥራዎች የነበረውን አፈፃፀም አቅርበዋል።

ተቋሙ በኦፕሬሽን ዘርፍ ከ13 ሺህ ጌጋ ዋት ሰዓት በላይ ኃይል በማምረት የዕቅዱን 115 ነጥብ 6 በመቶ ማሳካቱን የገለፁት አቶ ህይወት ይህም ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር የ40 ነጥብ 2 በመቶ ዕድገት አሳይቷል ብለዋል።

ባለፉት 6 ወራት ለሀገር ውስጥ ደንበኞች 11 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር፣ በዶላር ለሚከፍሉ ደንበኞች 70 ነጥብ 6 ሚሊዮን ዶላር እና ለጎረቤት ሀገራት 61 ሚሊዮን ዶላር  ሽያጭ መከናወኑን ጠቅሰው 1 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር በታሪፍ ለውጥ ምክንያት የተገኘ መሆኑን በሪፖርቱ አመልክተዋል።

እንደ አቶ ህይወት ገለፃ የ2016 በጀት ዓመት የኦዲት ሪፖርት ንፁህ ሆኖ መገምገሙ፤ ለመጀመሪያ ጊዜ የስድስት ወራት የተቋም ፋይናንስ መዝጋት መቻሉ እና በውጭ ምንዛሬ የሚደረግ ግብይት መጨመሩ ባለፉት 6 ወራት ከተመዘገቡ መሻሻሎች መካከል ይጠቀሳሉ።

በተቋሙ የኮርፖሬት ፋይናንስና ሀብት አስተዳደር ዘርፍ ምክትል ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ደመረ አሰፋ እንደተናገሩት ተቋሙ 87 በመቶ የሚሆነው የፋይናንስ ገቢውን ወደፊት ሀብት ያመጣሉ ተብለው በሚታሰቡ ፕሮጀክቶች ላይ እያዋለ ይገኛል።

ባለፉት 6 ወራት የታየው የፋይናንስ ገቢ ዕድገት ከውጭ ምንዛሪ መሻሻል ጋር ተያይዞ የመጣ መሆኑንም ነው ምክትል ዋና ሥራ አስፈፃሚው ያብራሩት።

በተቋሙ የትራንስሚሽን ቢዝነስ ዘርፍ ምክትል ዋና ሥራ አስፈፃሚ ኢንጂነር አንዱዓለም ሲዓ በበኩላቸው ተቋሙን በዲጂታላይዜሽን መስኮች የማዘመንና የአሰራር ሥርዓቶችን የመዘርጋት ሥራዎች እየተከናወኑ ነው ብለዋል።

የተቋሙን ድረ-ገፅ ጨምሮ ሦስት የአሰራር ሥርዓቶችን የሚያዘምኑ ሶፍትዌሮች በራስ አቅም መዘጋጀታቸውንም ነው የገለፁት።

በኢትዮጵያ ኢንቨስትመት ሆልዲንግስ የኢነርጂና ኮኔክቲቪቲ ዘርፍ ፖርቲፎሊዮ ዳይሬክተር አቶ ቴዎድርስ ተገኘ እንደተናገሩት የኃይል ምርት ዕድገትና የአቅርቦት መሻሻሎች፣ ተቋሙን ለማዘመን እየተሠሩ ያሉ የለውጥ ሥራዎች፣ ወቅታዊ የሂሳብ መግለጫ ዝግጅት እንዲሁም ፕሮጀክቶችን በራስ አቅም የማከናወን ሥራዎች ተጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው ገልፀዋል።

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይልን የአፈፃፀም መለኪያ መስኮች ከኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ መለኪያዎች ጋር የማጣጣምና የማሻሻል ሥራዎች እንደሚሰሩም ነው የጠቆሙት።

ተቋሙ የገቢ አሰባሰብ ሥርዓቱ ላይ በትኩረት ሊሰራ እንደሚገባው የጠቀሱት አቶ ቴዎድሮስ ከሱዳን ጋር ተያይዞ ያልተከፈሉ ውዝፍ የኃይል ሽያጭ ገቢዎችን ለመሰብሰብ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በጋራ እንደሚሰራ ተናግረዋል።

በግምገማው ላይ የማጠቃለያ ሃሳብ የሰጡት የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ሥራ አስፈፃሚ ኢንጂነር አሸብር ባልቻ በበኩላቸው በተቋሙ ተተኪ አመራሮችን ከማፍራት አንፃር መመሪያ ተዘጋጅቶ ወደ ሥራ ተገብቷል ብለዋል።

እንደ ኢንጂነር አሸብር ገለፃ ከኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ ጋር በትብብር በመስራት በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ የሆነ ተቋም ለመፍጠር በትኩረት ይሰራል።

የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይልን ማስተዳደር ከጀመረ ወዲህ ይህ የአፈፃፀም ግምገማ የመጀመሪያው ነው።
? “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”

Scroll to Top