የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል በውሃ ኃይል ማመንጫ ዘርፍ የሰለጠነ ባለሙያ ለማፍራት የሚያስችለውን የመግባቢያ ስምምነት ቮይት ሀይድሮ ከተሰኘ የጀርመን ኩባንያ ጋር ተፈራርሟል።
ስምምነቱን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ሥራ አስፈፃሚ ኢንጂነር አሸብር ባልቻ እና በቮይት ሀይድሮ ኩባንያ የሀይድሮ ሰርቪስ እና አውቶሜሽን ኃላፊ ሚስተር አሎይስ ታግሊበር ተፈራርመዋል፡፡
ኢንጂነር አሸብር በፊርማ ሥነስርዓቱ ላይ እንደተናገሩት ተቋሙ በአሁኑ ወቅት እያመነጨ ካለው የኤሌክትሪክ ኃይል 92 በመቶ የሚሆነው ከውሃ የሚገኝ በመሆኑ ስምምነቱ በዘርፉ ብቃት ያለው የሰው ኃይል ለማፍራት ያግዛል፡፡
ኩባንያው ያለውን የካበተ ልምድ ለተቋሙ ለማካፈል እያደረገ ያለውን ጥረት አመስግነው ስምምነቱ ከኩባንያው ጋር ያለውን ግንኙነት እንደሚያጠናክረውም አስታውቀዋል፡፡
የአቅም ግንባታ ሥራው ውጤታማ እንዲሆን ኩባንያው አቅም ያላቸው ባለሙያዎች በመመድብ እንዲሰራ አሳስበዋል፡፡
በቮይት ሀይድሮ ኩባንያ የሀይድሮ ሰርቪስ እና አውቶሜሽን ኃላፊ ሚስተር አሎይስ ታግሊበር በበኩላቸው ኩባንያቸው ከተቋሙ ጋር በተለያዩ ዘርፎች በጋራ ሲሰራ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡
በውሃ ኃይል ማመንጫዎች ላይ ለተቋሙ ባለሙያዎች የአቅም ግንባት ለመስጠት የተደረሰው ስምምነት በአቅም ግንባታ ጉዳዮች ላይ ከተቋሙ ጋር ለመስራት አዲስ ምዕራፍ የሚከፍት መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
ኩባንያቸውው በውሃ ኃይል ማመንጫዎች ላይ ያለውን ልምድ እና እውቀት ለተቋሙ ለማከፈል ዝግጁ መሆኑን አንስተው ለዚህም ብቃት ያላቸው ባለሙያዎችን በመመደብ እንደሚሰራ አረጋግጠዋል፡፡
በኃይል ማመንጫ ጣቢያዎች ኦፕሬሽን ዘርፍ የቴክኒካል ድጋፍ ቢሮ ሥራ አስኪያጅ አቶ አብዱ ይማም እንደተናገሩት ስምምነቱ በውኃ ኃይል ማመንጫዎች ላይ ከዲዛይን ጀምሮ ማመንጫዎች አገልግሎት መስጠት እስከሚያቆሙበት (decommissioning) ባለው የአሰራር ሂደት ላይ የአቅም ግንባታ ስልጠና ለመስጠት ያለመ ነው፡፡
በስልጠናው ላይ ከጀነሬሽን ኦፕሬሽን ዘርፍ እና ከኢንጂነሪንግ ዘርፍ የጀነሬሽን ዲዛይን የሥራ ክፍል የተውጣጡ 80 ባለሙያዎችና የሥራ ኃላፊዎች እንደሚሳተፉበት ጠቁመዋል፡፡
የአቅም ግንባታ ለመስጠት የተካሄደው ስምምነት ለዘጠኝ ወራት የሚቆይ ሲሆን ለዚህም የአራት ሚሊዮን ዶላር ስምምነት ተደርጓል፡፡
? “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”







