የተቋሙ ሠራተኞች በመንግስት ውሳኔዎች እና አቅጣጫዎች ዙሪያ ተወያዩ

የተቋሙ ሠራተኞች በመንግስት ውሳኔዎች እና አቅጣጫዎች ዙሪያ ተወያዩ

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የሥራ መሪዎችና ሠራተኞች “ከቃል ወደ ባህል” በሚል መሪ ሀሳብ የብልፅግና ፓርቲ ባካሄደው ሁለተኛ መደበኛ ጉባዔ በተቀመጡ ውሳኔዎችና አቅጣጫዎች ዙሪያ ውይይት አካሂደዋል።

በውይይቱ ላይ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የተቋሙ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ኢንጂነር አሸብር ባልቻ እንደገለፁት ውይይቱ ሠራተኛው በጉባዔው በተቀመጡ ውሳኔዎችና ቀጣይ አቅጣጫዎች ላይ ግንዛቤ በመጨበጥ ለተግባራዊነቱ እንዲሰራ ለማድረግ ነው።

ፓርቲው መንግስትን የሚመራ እንደመሆኑ መጠን ሠራተኞችም የፓርቲውን ውሳኔዎችና ያስቀመጣቸውን የትኩረት አቅጣጫዎች በመረዳት  ሥራቸውን በዚሁ አግባብ ማከናወን እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።

በመድረኩ ላይ በፓርቲው ሁለተኛ ጉባዔ በተቀመጡ ውሳኔዎችና ቀጣይ አቅጣጫዎች ዙሪያ የተዘጋጀ ሰነድ በንባብ ቀርቧል።

ጠንካራ የፓርቲ ግንባታ፣ የብሔራዊነት ገዥ ትርክት ግንባታን ማጠናከር፣ ውጤታማ የሰላም ግንባታ ሥራ መስራት፣ የፍትህ ዘርፍ ውጤታማነትን ማሳደግ፣ የሀገር ግንባታን ማጠናከር እና የኢኮኖሚ ልማትን ማፋጠን የሚሉት በጉባዔው ከተቀመጡ ውሳኔዎችና አቅጣጫዎች መካከል መሆናቸው በሰነዱ ላይ ተመልክቷል።

በተጨማሪም ማህበራዊ ብልፅግናን የሚያረጋግጡ ሥራዎችን በውጤታማነት ማስቀጠል፣ ውጤታማ የዲፕሎማሲ ሥራዎች መስራት፣ የሲቪል ሰርቪስ ሪፎርም ውጤታማነትን ማረጋገጥ እና ጠንካራ የሚዲያና ኮሙዩኒኬሽን ሥራዎችን መስራት የሚሉ ውሳኔዎችና አቅጣጫዎች በፓርቲው መቀመጣቸውም ተገልጿል።

በውይይቱ ላይ ከሠላም፣ ከተቋም ግንባታና አገልግሎት አሰጣጥ፣ ከልማትና መልካም አስተዳደር እንዲሁም ከፍትህ ሥርዓቱ ጋር የተያያዙ ጥያቄዎች እና አስተያየቶች በተሳታፊዎች ቀርበዋል።

በተቋሙ የኮርፖሬት ፋይናንስ እና ሀብት አስተዳደር ዘርፍ ምክትል ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ደመረ አሰፋ በሰጡት ምላሽ የመንግስት የልማት ድርጅቶች በመንግስት ፖሊሲና የፖለቲካ አቅጣጫዎች የሚመሩ መሆናቸውን ገልፀዋል።

መንግስት የግጭት መንስዔዎችን ከምንጩ ለማድረቅና የሀገሪቱን ሀብት በፍትሐዊነት ለመጠቀም በትኩረት እየሰራ መሆኑን አቶ ደመረ ጠቅሰዋል።

የሰላም ጉዳይ ለመንግስት ብቻ የተተወ ባለመሆኑ ሁላችንም ሰላምን ለማጽናት የድርሻችንን ልንወጣ ይገባል ነው ያሉት።

በተቋሙ የትራንስሚሽን ዘርፍ ምክትል ዋና ሥራ አስፈፃሚ ኢንጂነር አንዱዓለም ሲዓ በበኩላቸው ገዢ ሀገራዊ ትርክት ለመገንባት የጋራ መግባባት መፍጠር ወሳኝ መሆኑን አንስተዋል።

መንግስት ከሰላም እጦት ጋር የተያያዙ ችግሮችን አካታች በሆነ መልኩ ለመፍታት ሥር ነቀል ለውጥ ለማምጣት እየሰራ መሆኑን ገልፀዋል።

የኢንጂነሪንግ እና ግንባታ ዘርፍ ምክትል ዋና ሥራ አስፈፃሚ ኢንጂነር ውድነህ የማነ በበኩላቸው ውይይት የተደረገበት ሰነድ የፓርቲ ብቻ ሳይሆን የመንግስት ሰነድ በመሆኑ፣ እንደዜጋ ማወቅና  በተቀመጠው አቅጣጫ መሰረት መፈፀም ስለሚጠበቅብን ነው ብለዋል።

? “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”

Scroll to Top