የማከፋፈያ ጣቢያውን አቅም ለማሳደግ የሚያስችሉ ሥራዎች ለውጥ አምጥተዋል

የማከፋፈያ ጣቢያውን አቅም ለማሳደግ የሚያስችሉ ሥራዎች ለውጥ አምጥተዋል

የጅግጅጋ ባለ 132 ኪሎ ቮልት የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያን አቅም ለማሳደግ የሚያስችሉ ሥራዎች  እየተከናወኑ መሆኑን የጣቢያው ሥራ አስኪያጅ አስታወቁ።

ሥራ አስኪያጁ አቶ ደምለው ተሾመ እንደገለፁት እየተከናወነ የሚገኘው የጂ.አይ.ኤስ ስዊችጊር ቅየራ ሥራ የማከፋፈያ ጣቢያውን የኦፕሬሽን አቅም ለማዘመን የሚያግዝ ነው።

በአሁኑ ወቅት በማከፋፈያ ጣቢያው ለረጅም ዓመታት አገልግሎት ሲሰጡ የቆዩትን የ15 እና 33 ኪሎ ቮልት ስዊችጊሮች በሌላ ዘመናዊ መቆጣጠሪያዎች የመቀየር ሥራ መሰራቱንም ነው የተናገሩት።

የጅግጅጋ ማከፋፈያ ጣቢያ ከዓመት በፊት ከ17 ሜጋ ዋት ያልበለጠ ኃይል የመጫን አቅም እንደነበረው የገለፁት ሥራ አስኪያጁ በ15 እና 33 ኪሎ ቮልት ስዊችጊሮች ላይ በተከናወነው የአቅም ማሳደግ ሥራ ሳቢያ ኃይል የማቅረብ አቅሙ ከ24 ሜጋ ዋት በላይ ከፍ ማለቱን ጠቅሰዋል።

እንደ ሥራ አስኪያጁ ገለፃ በተደረገው የአቅም ማሳደግ ሥራ ቀደም ሲል በ15 ኪሎ ቮልት አራት የነበሩ ወጪ መስመሮችን ወደ አምስት እንዲሁም በ33 ኪሎ ቮልት አራት የነበሩ ወጪ መስመሮችን ወደ ስድስት ማሳደግ ተችሏል።

በአየር ሲሰራ የቆየው መቆጣጠሪያ (vacume switchgear ) በዘመናዊ መቆጣጠሪያ በመቀየሩ የኃይል መቆራረጥንና በጥገና ሥራዎች ላይ ሊያጋጥሙ የሚችሉ ችግሮችን በመቅረፍ የኦፕሬሽንና የጥገና ሥራዎችን በቀላሉ ለማከናወን እንደሚረዳ ነው ሥራ አስኪያጁ የጠቆሙት።

በ2016 በጀት ዓመት በጣቢያው 31 ነጥብ 5 ሜጋ ቮልት አምፔር አቅም ያለው ተጨማሪ ትራንስፎርመር ማስቀመጥ ቢቻልም በ15 እና 33 ኪሎ ቮልት ስዊችጊሮች የአቅም ውስንነት የተነሳ የሚፈለገውን ኃይል ለተጠቃሚው ህብረተሰብ ማድረስ እንዳልተቻለ አስታውሰዋል።

በ1997 ዓ.ም አገልግሎት መስጠት የጀመረው የጅግጅጋ ማከፋፈያ ጣቢያ በ132 ኪሎ ቮልት ከሐረር ቁጥር ሦስት ኃይል ተቀብሎ በባለ 33 ኪሎ ቮልት  ለቀብሪበያህ፣ ቶጎ ውጫሌ፣ ጭናክሰን፣ ፋፈን እና በጅግጅጋ ዙሪያ ለሚገኙ ከተሞችና አካባቢዎች እንዲሁም በባለ 15 ኪሎ ቮልት አራት ለጅግጅጋ ከተማ ኃይል እያቀረበ ይገኛል።

? “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”

Scroll to Top