ሪጅኑ አስተማማኝ ኃይል ተደራሽ ለማድረግ የሚያስችሉ ሥራዎች ማከናወኑን ገለፀ

ሪጅኑ አስተማማኝ ኃይል ተደራሽ ለማድረግ የሚያስችሉ ሥራዎች ማከናወኑን ገለፀ

የምስራቅ ሁለት ሪጅን የማስተላለፊያ መስመሮችና ማከፋፈያ ጣቢያዎች ኦፕሬሽን መምሪያ ባለፉት ስድስት ወራት አስተማማኝ የኃይል አቅርቦት ተደራሽ ለማድረግ የሚያስችሉ ሥራዎች ማከናወኑን አስታወቀ።

የመምሪያው ተወካይ ዳይሬክተር አቶ ወርቁ ሙሉ እንደገለፁት በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያዎቹ ስድስት ወራት በጅግጅጋ፣ ፊቅ፣ ጎዴ፣ ደገሃቡር እና ቀብሪደሃር  የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያዎች ላይ የአስቸኳይ ጥገና እና የፍተሻ ሥራዎች ተሰርተዋል።

ሪጅኑ የኃይል አቅርቦቱን ይበልጥ አስተማማኝ ለማድረግ በጅግጅጋ የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያ ላይ የአቅም ማሳደግ ሥራዎች ማከናወኑን ጠቁመዋል።

በአሁኑ ወቅት የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያው ለጅግጅጋ ከተማና አካባቢው አስተማማኝ የኤሌክትሪክ ኃይል እያቀረበ እንደሚገኝ የጠቀሱት ተወካይ ዳይሬክተሩ በጣቢያው ከተሰራው የ15 እና 33 ኪሎ ቮልት ስዊችጊር የማዘመን ሥራ ባሻገር የትራንስፎርመር አቅም ለማሳደግ የሚያስችሉ ጥያቄዎች ለተቋሙ የሪጅኖች ማስተባበሪያ መምሪያ መቅረቡን ተናግረዋል።

በቀጣይም በጎዴ የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያ ላይ የዘመናዊ ስዊችጊር ቅየራ ሥራ ለማከናወን ታቅዶ እንቅስቃሴዎች መጀመራቸውንም ነው አቶ ወርቁ የገለፁት።

እንደ ተወካይ ዳይሬክተሩ ገለፃ ሪጅኑ በስሩ በሚያስተዳድራቸው አምስት የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያዎች እና የማስተላለፊያ መስመሮች በዕቅድ ላይ የተመሰረቱ የጥገና እና የፍተሻ ሥራዎች እያከናወነ ይገኛል።

በዚህም በግማሽ በጀት ዓመቱ በአምስቱ የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያዎች ላይ 85 ቤዮችን የመጠገን እና የመፈተሽ ሥራ መስራቱን ተናግረዋል፡፡

ሪጅኑ በሚያስተዳድራቸው የማስተላለፊያ መስመሮች ላይ 1 ሺ 643 የኃይል ተሸካሚ ምሰሶ ብረቶች ላይ እንዲሁም 719 ኪሎ ሜትር የሚሸፍን የፍተሻና ጥገና ሥራዎች መከናወናቸውንም ነው አቶ ወርቁ ያብራሩት።

እንደ ተወካይ ዳይሬክተሩ ገለፃ በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያዎቹ ስድስት ወራት በተከናወኑ የጥገና እና የፍተሻ ሥራዎች በተደጋጋሚ ይከሰት የነበረውን የኃይል መቆራረጥ እንዲቀንስ አስችሏል።

በጎዴ የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያ ደረጃውን የጠበቀ የአጥር ግንባታ ሥራ በመከናወን ላይ እንደሚገኝ የተናገሩት አቶ ወርቁ የአጥር ግንባታው በአካባቢው የሚንቀሳቀሱ ግመሎች ወደ ጣቢያው እንዳይገቡ ለመከላከል ያለመ መሆኑንም ነው የገለፁት።

ባለፉት ስድስት ወራት የጅግጅጋ ኃይል ማከፋፈያ ጣቢያ የኦፕሬሽን ሠራተኞች መኖሪያ ቤት ዕድሳት መከናወኑን ጠቅሰው በቀጣይም የቀብሪድሃር እና ደጋሃቡር የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያ የኦፕሬሽን ሠራተኞች የመኖሪያ ቤት ዕድሳት ለማከናወን የግዥ ሂደቱ መጠናቀቁን አብራርተዋል።

ሪጅኑ በጅግጅጋ የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያ ውስጥ በተቋሙ የራስ ኃይል የግንባታ መምሪያ በኩል ጊዜያዊ ተገጣጣሚ የቢሮ ግንባታ ለማከናወን አቅዶ በስፋት እየተንቀሳቀሰ እንደሚገኝም ነው የተናገሩት።

? “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ይፋዊ የማኅበራዊ ትስስር ገጾችን በመቀላቀል ትኩስ መረጃዎችን በፍጥነት ያግኙ
ፌስቡክ↠ https://www.facebook.com/Ethioelectric
ቴሌግራም↠ https://t.me/EEPCommuication
ትዊተር ↠ https://twitter.com/EEPethiopia
ዩትዩብ ቻናል↠ https://www.youtube.com/@ethiopowermedia
ቲክቶክ አካውንት↠https://tiktok.com/@ethio_power
ድረ – ገፃችንንም ይጎብኙ www.eep.com.et
የካቲት 14  ቀን 2017 ዓ.ም

Scroll to Top