በመንግስት እና በግል አጋርነት የሚለሙ ስምንት የፀሐይ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶች መለየታቸውን በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የመንግሥት እና የግል አጋርነት መመሪያ ገለፀ።
በመምሪያው የፀሐይና ንፋስ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶች ሥራ አስኪያጅ አቶ አሸናፊ ዘውዴ እንደገለጹት የኃይል ስብጥሩን በማሳደግ የኤሌክትሪክ ተደራሽነትን ለማስፋት በኃይል ማመንጨት ዘርፍ የግል አልሚዎች እንዲሳተፉ የሚያስችል የሕግ ማዕቀፍ ተዘጋጅቷል፡፡
የግል ዘርፉ ኃይል ማመንጫ ገንብቶና ኃይል አመንጭቶ ለተቋሙ መሸጥ አዲስ አሰራር በመሆኑ የፕሮጀክቶችን አዋጭነት በተመለከተ ተቋሙ የግል ዘርፉን ለማሳተፍና ለማበረታታት ብሎም ፕሮጀክቶቹን ሥራ ላይ ለማዋል የሚያስችል ጥናት በዓለም አቀፍ የፋይናንስ ኮርፖሬሽን መሰራቱን ተናግረዋል፡፡
በዚህም በመንግስትና በግል አጋርነት የሚለሙ ስምንት የፀሐይ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶች መለየታቸውንና ከእነዚህ ውስጥ የአራቱ ማለትም ጋድ 1 እና 2፣ ዲቼቶ እና ወራንሶ ጥናታቸው መጠናቀቁንም አብራርተዋል፡፡
በጥናት የተለዩትን የፀሐይ ኃይል ማመንጫዎች ለማልማት እ.ኤ.አ በ2019 ግንቦት ወር ጨረታ መውጣቱን አቶ አሸናፊ አስታወሰዋል፡፡
ይሁንና በወቅቱ የውጭ ምንዛሪ አቅርቦት ዋስትና በመጠየቁ፣ በውጭ ሀገር ፕሮጀክቱን የተመለከተ የገንዘብ ዝውውር ለማከናወን አካውንት የመክፈት ፈቃድ በመጠየቁ እና ይህንን ለማስፈጸም የሚያስችል አዲስ መመሪያ በማስፈለጉ የግል አልሚዎቹ ወደ ተግባር አለመግባታቸውን ጠቁመዋል፡፡
አሁን ላይ ግን በሀገሪቱ እየተተገበረ በሚገኘው የኢኮኖሚ ማሻሻያ ፖሊሲ ላይ መንግስት ለፕሮጀክቶቹ ትኩረት በመስጠቱ፣ የውጭ ምንዛሬ አቅርቦት ዋስትና በመተግበሩ እና የውጭ ምንዛሬ አካውንት ለመክፈት አስቻይ ሁኔታ በመኖሩ ፕሮጀክቶቹን ወደ ትግበር እንዲገቡ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በዚህም ጋድ 2 እና ወራንሶ የፀሐይ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶችን በመንግስት እና በግል አጋርነት ለማልማት ጨረታ ወጥቷል ብለዋል፡፡
ሁለቱ የፀሐይ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶች 225 ሜጋ ዋት የማመንጨት አቅም እንዳላቸውና ፕሮጀክቶቹን ለማጠናቀቅ 200 ሚሊዮን ዶላር እንደሚያስፈልግ አብራርተዋል፡፡
ፕሮጀክቶቹ ሲጠናቀቁ የኃይል ስብጥሩን በማሳደግ የኤሌክትሪክ ተደራሽነቱን ከማስፋትም ባሻገር መንግስት ፕሮጀክቱን በራሱ የፋይናንስ አቅም ቢሰራ ሊያወጣ የሚችለውን ፋይናንስ በግል አልሚው በመሸፈን ፕሮጀክቶቹን መተግበር የሚያስችለው መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ፕሮጀክቶቹ በመንግስትና ግል አጋርነት ሲለሙ በተሻለ ጥራትና ጊዜ ለማጠናቀቅ ዕድል ይፈጥራል ያሉት ሥራ አስኪያጁ ከአዋጭነት ጥናቱ ጀምሮ እስከ ፕሮጀክቱ ትግበራ የእውቀት ሽግግር እንዲኖር ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡
ከስምንቱ የፀሐይ ኃይል ማመንጫዎች እስከ 750 ሜጋ ዋት ለማመንጨት ዕቅድ ተይዟል፡፡
? “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ይፋዊ የማኅበራዊ ትስስር ገጾችን በመቀላቀል ትኩስ መረጃዎችን በፍጥነት ያግኙ
ፌስቡክ↠ https://www.facebook.com/Ethioelectric
ቴሌግራም↠ https://t.me/EEPCommuication
ትዊተር ↠ https://twitter.com/EEPethiopia
ዩትዩብ ቻናል↠ https://www.youtube.com/@ethiopowermedia
ቲክቶክ አካውንት↠https://tiktok.com/@ethio_power
ድረ – ገፃችንንም ይጎብኙ www.eep.com.et
የካቲት 14 ቀን 2017 ዓ.ም