በራስ ኃይል የሚከናወኑ ፕሮጀክቶች በተያዘላቸው ጊዜ እንዲጠናቀቁ ዋና ሥራ አስፈጻሚው አሳሰቡ

በራስ ኃይል የሚከናወኑ ፕሮጀክቶች በተያዘላቸው ጊዜ እንዲጠናቀቁ ዋና ሥራ አስፈጻሚው አሳሰቡ

በራስ ኃይል የሚከናወኑ ፕሮጀክቶችን በተያዘላቸው ጊዜና በጀት ማጠናቀቅ እንደሚገባ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ሥራ አስፈጻሚ አሳሰቡ፡፡

ዋና ሥራ አስፈፃሚው ኢንጂነር አሸብር ባልቻ ከተቋሙ የሥራ ኃላፊዎች ጋር በመሆን በራስ ኃይል የሚከናወኑ የማስተላለፊያ መስመሮችና ማከፋፈያ ጣቢያዎች ያሉበትን ደረጃ ገምግመዋል፡፡

ኢንጂነር አሸብር በዚሁ ወቅት እንዳሉት በተቋሙ የራስ ኃይል የሚከናወኑ የማስተላለፊያ መስመሮችና ማከፋፈያ ጣቢያዎች የተቋሙ የመፈጸም አቅም የሚገነባባቸው ከመሆናቸውም በተጨማሪ በጥራትና በጊዜ በማጠናቀቅ በዘርፉ ተወዳዳሪ ለመሆን ዕድል የሚሰጥ ነው ፡፡

የተቋሙ አብዛኛው በጀት በፕሮጀክቶች ላይ እንደሚውል የጠቆሙት ኢንጂነር አሸብር በሥራ ሂደት እያጋጠሙ ያሉ ችግሮች ላይ ተወያይቶ ቀጣይ የትኩረት አቅጣጫዎችን ለማስቀመጥ እና አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ ውይይቱ ማስፈለጉን ተናግረዋል፡፡

በራስ ኃይል በግንባታ ላይ የሚገኙ ፕሮጀክቶችን በተያዘላቸው ጊዜና በጀት እንዲሁም በተቀመጡ ዝርዝር መስፈርቶች መሰረት እንዲጠናቀቁ ለማድረግ በሥራው ላይ የሚሳተፉ አካላት ተቀናጅተው መስራት እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡

የኢንጂነሪንግና ኮንስትራክሽን ዘርፍ ሥራ አስፈጻሚ አቶ ውድነህ የማነ በበኩላቸው በተቋሙ በራስ ኃይል መምሪያ አስር የሚሆኑ የማስተላለፊያ መስመሮችና ማከፋፍያ ጣቢያዎች ግንባታ በመካሄድ ላይ ይገኛሉ ብለዋል፡፡

ውይይቱ በራስ ኃይል የሚሰሩ ፕሮጀክቶችን አፈጻጸም በመገምገም ከአስተሳሰብ ጀምሮ አሰራሮችን በመለወጥ እንዲሁም ፕሮጀክቶችን አቅዶ ከመፈፀም፣ ከፋይናንስ እና ከዕቃ አቅርቦት በተያያዘ እያጋጠሙ ያሉ ችግሮች በመቅረፍ አፈጻጸማቸውን ለማሻሻል እንደሚያግዝ ገልጸዋል፡፡

ቀደም ሲል የራስ ኃይል ግንባታና ማማከር የሥራ ክፍሎች ለየብቻ የነበሩ መሆኑን ያስታወሱት አቶ ውድነህ በመዋቅሩ ሁለቱ ክፍሎች በአንድ ላይ መሆናቸው ከዲዛይን ጀምሮ የግንባታ ሥራዎች በተቀናጀ መልኩ እንዲከናወኑ ያስችላል ብለዋል፡፡

እንደ ሥራ አስፈጻሚው ገለጻ የኢንጂነሪንግ ክፍሉ እንደ ተቆጣጣሪ ሳይሆን የኮንስትራክሽን ኃይሉ የሚፈልገውን ቴክኒካዊ ድጋፍ ለመስጠት ዕድል የሚሰጥ በመሆኑ ፕሮጀክቶች በጥራት፣ በጊዜና በተያዘላቸው በጀት ለማጠናቀቅ ይረዳል፡፡

በውይይቱ የፕሮጀክቶችን አፈፃፀም በመገምገም የሚስተዋሉ ችግሮች ተለይተው የሚፈቱበት ቀጣይ አቅጣጫ እንደሚቀመጥም ጠቁመዋል፡፡

ፕሮጀክቶችን በጊዜ ማጠናቀቅ ለተቋም ብሎም ለሀገር የሚኖረውን ሚና ከግምት በማስገባት ሁሉም ተቀናጅቶ መስራት እንደሚኖርበትም አሳስበዋል፡፡

? “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ይፋዊ የማኅበራዊ ትስስር ገጾችን በመቀላቀል ትኩስ መረጃዎችን በፍጥነት ያግኙ
ፌስቡክ↠ https://www.facebook.com/Ethioelectric
ቴሌግራም↠ https://t.me/EEPCommuication
ትዊተር ↠ https://twitter.com/EEPethiopia
ዩትዩብ ቻናል↠ https://www.youtube.com/@ethiopowermedia
ቲክቶክ አካውንት↠https://tiktok.com/@ethio_power
ድረ – ገፃችንንም ይጎብኙ www.eep.com.et
የካቲት 13  ቀን 2017 ዓ.ም

Scroll to Top