የተሽከርካሪ ጥገናን በዘመናዊ አሰራር በመታገዝ ለማከናወን የሚያስችል ዝግጅት እያደረገ መሆኑን በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የተሽከርካሪ አስተዳደር መምሪያ ገለፀ።
መምሪያው የተሽከርካሪ ጥገናን በሳፕ ቴክኖሎጅ በመታገዝ ለማከናወን የሚያስችል ስልጠና ለተሽከርካሪ ጥገና አስተዳደር ባለሙያዎችና የሥራ ኃላፊዎች እየሠጠ ይገኛል።
ስልጠናውን በንግግር ያስጀመሩት በተቋሙ የተሽከርካሪ አስተዳደር መምሪያ ዳይሬክተር አቶ ኃይላይ ተስፋይ እንደገለፁት የሁለተኛው ምዕራፍ የሳፕ ትግበራ አካል የሆነውን የተሽከርካሪና ማሽነሪ ጥገናና አስተዳደር ማኑዋልን በአግባቡ ለመተግበር ለባለሙያዎች ሥልጠና መስጠት ያስፈልጋል፡፡
ስልጠናው ከዚህ በፊት በማኑዋል ሲከናወን የነበረውን የተሽከርካሪ የጥገና ሥራ በዘመናዊ የአሰራር ስርዓት በመታገዝ ለማከናወን እንደሚያስችል ተናግረዋል::
እንደ አቶ ኃይላይ ገለፃ ሞጁሉ ተግባራዊ ሲደረግ የቅድመ መከላከል ጥገና እና በአጋጣሚ የሚከሰቱ የሥራ ላይ ብልሽት ጥገና ሥራዎችን በቀላሉ ለማከናወን ይረዳል።
የአሰራር ስርዓቱ ለተሸከርካሪዎች በወቅቱ የጥገና አገልግሎት እንዲያገኙ በማድረግ የአገልግሎት ጊዜያቸውን ለማራዘም፣ የአደጋ ተጋላጭነትን ለመቀነስ፣ የመረጃ አያያዝን ለማሳደግ እና በየጊዜው የሚስተዋሉ ብልሽቶችን በማስቀረት ለተሽከርካሪ ጥገና የሚወጣውን ወጭ ለመቀነስ እንደሚያግዝ አቶ ኃይላይ አስረድተዋል።
ሞጁሉ ሥራዎችን በቀላሉ ለማከናወን እንደሚያግዝ በመገንዘብ ሰልጣኞች ስልጠናውን በአግባቡ በመከታተል ለተግባራዊነቱ የበኩላቸውን ሚና መወጣት እንደሚጠበቅባቸውም ዳይሬክተሩ አሳስበዋል፡፡
ሥልጠናውን እየሰጡ የሚገኙት በተቋሙ የተሸከርካሪ ጥገና አስተዳደር ባለሙያ የሆኑት አቶ ብርሃኑ ታፈሰ በበኩላቸው ስልጠናው ከተሸከርካሪ ጥገና ጋር በተያያዘ የሚያገለግሉ መረጃዎችን በአሰራር ስርዓቱ እንዴት ማስገባት እንደሚቻል እና በጥገና ሂደቶቹ ላይ ትኩረት ያደርጋል ብለዋል፡፡
የአሰራር ስርዓቱ የተሸከርካሪዎችን አጠቃላይ መረጃዎች፣ በጥገና ሥራዉ ላይ ምን ሥራዎች እንደሚከናወኑ፣ ተሸከርካሪው በማን ሥር እንደሚገኝና ጥገና የት እንደሚደረግለት እንዲሁም የሚከናወኑ የጥገና አይነቶችንና ጥገናው የሚካሄድበትን ጊዜ እንደሚያሳውቅ አቶ ብርሃኑ አስረድተዋል፡፡
ለአምስት ቀናት በሚቆየው ስልጠና ላይ አስራ ስድስት የተሽከርካሪ ጥገና አስተዳደር ባለሙያዎች እና የሥራ ኃላፊዎች እየተሳተፉ ሲሆን በቀጣይ ለኃይል ማመንጫ ጣቢያዎች እና ለሪጅን የተሸከርካሪ ጥገና ባለሙያዎች ተመሳሳይ ስልጠና ለመስጠት መታቀዱ ተገልጿል።
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል በአሁኑ ወቅት ከ1 ሺ 200 በላይ ተሽከርካሪዎችና ማሽነሪዎች ያስተዳድራል።
? “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”





