የባህርዳር-ወልዲያ-ኮምቦልቻ ባለ 400 ኪሎ ቮልት የከፍተኛ ኃይል ማስተላለፊያ መስመር ፕሮጀክት የተለያዩ ፈታኝ ሁኔታዎችን በፅናት በማለፍ ወደ ማጠናቀቂያው ምዕራፍ መሸጋገሩ ተገልፀ
የፕሮጀክቱ ሥራ አስኪያጅ አቶ አሸናፊ ሙሉ ብርሃን እንደገለፁት ከባህርዳር እስከ ወልዲያ ያለውን 296 ኪሎ ሜትር የሚረዝመውን የፕሮጀክት አካል ለማጠናቀቅ በአሁን ወቅት የቀረው 5 ኪሎ ሜትር ብቻ ነው።


ፕሮጀክቱ በተያዘው በጀት ዓመት ሙሉ በሙሉ ተጠናቆ ከኃይል ጋር እንዲገናኝ ከፍተኛ ርብርብ እየተደረገ ባለበት በዚህ ወቅት በሰሜን ወሎ ዞን መቄት ወረዳ ልዩ ስሙ አግሪት በተባለ አካባቢ በሰባት የኃይል ተሸካሚ ምሰሶዎች (ታወሮች) እና በ2 ነጥብ 5 ኪሎ ሜትር በሚገመት ኮንዳክተር ላይ ጉዳት አጋጥሟል። ይህ የደረሰው ጉዳት በቀሪ ስራዎች ላይ የራሱን ተፅዕኖ አሳድሯል።
ይሁን እንጂ የፕሮጀክት ቢሮው ሥራውን ከሚያከናውነው የሥራ ተቋራጭ ጋር በአስቸኳይ በመቀናጀት የተጎዱትን ኮንዳክተሮች ተክቶ እንደገና ለመዘርጋትና የፕሮጀክቱን የማጠናቀቂያ ጊዜ በማያስተጓጉል መልኩ ሰርቶ ለማጠናቀቅ ከፍተኛ ርብርብ እያደረገ መሆኑን አቶ አሸናፊ ገልፀዋል።
የፕሮጀክቱ መጠናቀቅ ለአካባቢው ማህበረሰብ አስተማማኝ ኃይል ለማቅረብ እና ለኢንዱስትሪ መስፋፋት ዋነኛ ምሰሶ መሆኑን የገለፁት ሥራ አስኪያጁ ማህበረሰቡና ባለድርሻ አካላት በአካባቢያቸው ለሚገነቡ ፕሮጀክቶች ጥበቃ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።
በባህርዳር-ወልዲያ-ኮምቦልቻ የከፍተኛ ኃይል ማስተላለፊያ መስመር ፕሮጀክት ላይ በተለያዩ ጊዜያት የሚደርሱ ጉዳቶች የፕሮጀክቱን አፈፃፀም እንዲጓተት አድርጓል። ይህ ድርጊት ህዝቡ በተያዘለት ጊዜ የኃይል ተጠቃሚ እንዳይሆን ከማድረጉም በላይ ተቋሙንና አገርን ለከፍተኛ የገንዘብ እና የጊዜ ኪሳራ መዳረጉን ሥራ አስኪያጁ ተናግረዋል።


