ተቋሙ የኃይል አቅርቦትን ለማስፋት በርካታ ስራዎች እያከናወነ ነው

ተቋሙ የኃይል አቅርቦትን ለማስፋት በርካታ ስራዎች እያከናወነ ነው

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች የኃይል አቅርቦት ተደራሽነትን ለማስፋት በርካታ ስራዎችን እያከናወነ መሆኑን አስታወቀ።

በተቋሙ የኮርፖሬት ኮሙዩኒኬሽን መምሪያ ዳይሬክተር ተወካይ ወ/ሮ ሃይማኖት ገበየሁ እንደተናገሩት ተቋሙ ከደብረ ማርቆስ እስከ ባህር ዳር ባለው ኮሪደር ላይ የተለያዩ የኃይል መሠረተ ልማት ግንባታዎችን እያከናወነ ይገኛል።

ከተከናወኑ ተግባራት መካከልም የደጀን – ደብረ ማርቆስ የ230 ኪሎ ቮልት ማከፋፈያ እና ማስተላለፊያ መስመር ግንባታ በቅርቡ ተጠናቆ ወደ ሥራ መግባቱ በዋና ማሳያነት ተጠቃሽ ነው።

በዚሁ ኮሪደር ውስጥ እየተገነባ የሚገኘውና አጠቃላይ አፈፃፀሙ ከ55 በመቶ በላይ የደረሰው የቡሬ አግሮ ኢንዱስትሪ ባለ 230 ኪ.ቮ የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያ ሌላኛው ማሳያ መሆኑን ወ/ሮ ሃይማኖት ገልፀዋል።

ከዚህ በተጨማሪም በፕራይም-1 (PRIME) ፕሮግራም ማዕቀፍ ስር ከዓለም ባንክ በተገኘ የ19 ነጥብ 9 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ብድር ተቋሙ በእንጅባራ ከተማ አዲስ የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያና የማስተላለፊያ መስመር ለመገንባት ማቀዱን አስታውቀዋል።

ይህ በእንጅባራ ከተማ የሚገነባው ባለ 230 ኪ.ቮ አዲስ ፕሮጀክት በአሁኑ ወቅት ግንባታ ላይ ካለው የቡሬ አግሮ ኢንዱስትሪ የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያ የሚነሳና የ35 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው ጥምር ባለ 230 ኪ.ቮ የኃይል ማስተላለፊያ መስመር ግንባታ የሚኖረው መሆኑን ተወካይዋ አብራርተዋል።

የግንባታ ስራውን በ2019 በጀት ዓመት ለመጀመር የታቀደ ሲሆን ሙሉ የፕሮጀክት ስራውን ከ18 እስከ 24 ወራት ባለው ጊዜ ውስጥ ለማጠናቀቅ ዕቅድ ተይዞ እየተሰራ ይገኛል።

እስካሁንም የፕሮጀክቱን የግንባታ ሥራ በቀጥታ ለመጀመር የሚያስችሉ እንደ የመስመር ቅየሳ፣ የቦታ መረጣ፣ የአፈር ምርመራ እና የአካባቢያዊ ተፅዕኖ ጥናት ግምገማዎች ያሉ የቅድመ ዝግጅት ስራዎች ሙሉ በሙሉ ተጠናቀው ዝግጁ ሆነዋል።

ፕሮጀክቱ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል በባለቤትነት የሚያከናውን ቢሆንም ለስራው ስኬታማነት የክልሉ መስተዳድር አስፈላጊውን ድጋፍ እንዲያደርግም ተወካይዋ ጥሪያቸውን አቅርበዋል።

Scroll to Top