በማከፋፈያ ጣቢያ የተተከለው የጂአይኤስ (GIS) ቴክኖሎጂ የኦፕሬሽን ሥራዎችን እያቀላጠፈ ነው

በማከፋፈያ ጣቢያ የተተከለው የጂአይኤስ (GIS) ቴክኖሎጂ የኦፕሬሽን ሥራዎችን እያቀላጠፈ ነው

በበደሌ ባለ 230 ኪሎ ቮልት የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያ በሰኔ 2016 ዓ.ም የተተከለው የጂአይኤስ (GIS) መቆጣጠሪያ ብሬከር የኦፕሬሽንና የጥገና ሥራዎችን በማዘመን ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑን የጣቢያዉ ኃላፊ አቶ ሲሳይ ቀኖ ተናገሩ

በቡኖ በደሌ ዞን የሚገኛውና በ1981 ዓ.ም. አገልግሎት መስጠት የጀመረው ይህ የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያ የኤሌክትሪክ ብልሽትንና አደጋን ሙሉ በሙሉ በሚከላከለው በዚህ ዘመናዊ የጋዝ መቆጣጠሪያ ሥርዓት (GIS) በመታገዙ የአካባቢውን እያደገ የመጣ የኃይል ፍላጎት በአስተማማኝ ሁኔታ ማሟላት መቻሉን  ኃላፊው ተናግረዋል።

ጣቢያው ቀደም ሲል በነበረው አንድ ትራንስፎርመር ላይ የአቅም ማሳደግ ሥራዎችን በማከናወን አጠቃላይ የትራንስፎርመር ቁጥሩን ወደ አራት ያሳደገ ሲሆን ይህም ወደ ተለያዩ አካባቢዎች በቂ ኃይል ለማስተላለፍ ሰፊ ዕድል ፈጥሯል ብለዋል።

በአሁኑ ወቅት ጣቢያው በባለ 15 ኪሎ ቮልት ወጭ መስመሮች ለበደሌ ቢራ ፋብሪካ ለመቱ ዩኒቨርሲቲ በደሌ ካምፓስ፣ ለበደሌ ከተማ፣ ለስኳር ፋብሪካ እንዲሁም ለጨውራና ገቺ ወረዳዎች አስተማማኝ የኃይል አቅርቦት እያደለሰ ይገኛል ሲሉ አቶ ሲሳይ አብራርተዋል።

በተጨማሪም በባለ 33 ኪሎ ቮልት ወጭ መስመሮች አማካኝነት ለጫዋቃ፣ ለድጋና ለኮሎ ስሪ አካባቢዎች በቂ የኤሌክትሪክ ኃይል እያቀረበ ነው።

በአካባቢው የኤሌክትሪክ ፍላጎት በከፍተኛ ሁኔታ እያደገ የመጣ ሲሆን በ2014 ዓ.ም በ15 ኪሎ ቮልት መስመር ላይ 4 ነጥብ 5 ሜጋ ዋት የነበረው ከፍተኛ የኃይል ጭነት አሁን ላይ 8 ነጥብ 5 ሜጋ ዋት መድረሱን ኃላፊው ገልፀዋል።

የማከፋፈያ ጣቢያውን አገልግሎት ይበልጥ ዘመናዊና አስተማማኝ ለማድረግ ቀደም ሲል የነበሩት የባለ 33 ኪሎ ቮልት የቫኪዩም ብሬከሮች በአሁኑ ወቅት ወደ ጂአይኤስ ቴክኖሎጂ ተቀይረዋል ብለዋል።

ቀደም ሲል ሥራ ላይ የነበሩት የቫኪዩም ብሬከሮች ሠራተኞችን ለአደጋ የሚያጋልጡ፣ ለተደጋጋሚ ብልሽት የሚዳረጉ፣ ለጥገና ረጅም ጊዜ የሚወስዱና የኦፕሬሽን ሥራዎችን ውስብስብ ያደርጉ እንደነበር  ያስታወሱት አቶ ሲሳይ  አዲሱ የጂአይኤስ ብሬከር ግን እነዚህን ችግሮች ሙሉ በሙሉ በመቅረፍ የኦፕሬሽንና ጥገና ሥራዎችን እያቀላጠፈ ይገኛል ብለዋል።

ይህ ቴክኖሎጂ ሁሉም የአሠራር አካላቱ በአንድ ላይ የተገጠሙለት በመሆኑ ሁሉንም ሥራዎች በአንድ ቦታና ከርቀት በቀላሉ ለመቆጣጠር ከማስቻሉም በላይ የሠራተኞችን ደህንነት አስተማማኝ ማድረጉን ኃላፊው ገልፀዋል።

እንደ አቶ ሲሳይ ገለፃ ይህ ዘመናዊ የመቆጣጠሪያ ስርዓት በማሰራጫ መስመሮች ላይ የሚከሰቱ ብልሽቶችን ዓይነትና ትክክለኛ ቦታ በግልፅ ለይቶ ያሳያል። ይህም  የጥገና ሠራተኞች በፍጥነት ደርሰው ብልሽቱን እንዲያስተካክሉ ትልቅ እገዛ እያደረገ መሆኑን ገልፀዋል።

ቀደም ሲል የነበሩት የቫኪዩም ብሬከሮች መሸከም የሚችሉት 1.5 ሜጋ ዋት ብቻ የነበረ ሲሆን የጂአይኤስ ብሬከሮች ግን እያንዳንዳቸው እስከ 3 ሜጋ ዋት የመሸከም ከፍተኛ አቅም ያላቸው መሆኑን የጠቆሙት ኃላፊው ጣቢያው የትኛውንም ዓይነት ከፍተኛ የኃይል ፍላጎት ያለ ምንም መቆራረጥ እንዲያስተናግድ አስችሎታል ብለዋል።

ቴክኖሎጂው ሥራ ላይ ከዋለበት ጊዜ ጀምሮ ላለፉት ሁለት ዓመታት ምንም ዓይነት የቴክኒክ ብልሽትም ሆነ ጥገና ሳይሻው አገልግሎት እየሰጠ የሚገኝ ነው።

ይህም ተቋሙ ለጥገና ሥራ ያወጣ የነበረውን ወጭ ሙሉ በሙሉ አስቀርቶለታል። ጣቢያው በቀጣይም ቀሪዎቹን የ15 ኪሎ ቮልት የቫኪዩም ብሬከሮች ሙሉ በሙሉ ወደ ጂአይኤስ ቴክኖሎጂ ለመቀየርና ለህብረተሰቡ ይበልጥ ጥራት ያለው ኃይል ለማቅረብ በትኩረት እየሰራ መሆኑ ጭምር ኃላፊው ገልፀዋል።

Scroll to Top