ወድቀው የነበሩ የኃይል ተሸካሚ የብረት ምሰሶዎችን መልሶ የመትከል ሥራ ተጀመረ

ወድቀው የነበሩ የኃይል ተሸካሚ የብረት ምሰሶዎችን መልሶ የመትከል ሥራ ተጀመረ

በስርቆት ምክንያት ወድቀው የነበሩትን 17 የአዘዞ-ሸኽዲ ባለ 230 ኪሎ ቮልት የኃይል ማስተላለፊያ መስመር የብረት ምሰሶዎችን ከአንድ ዓመት በኋላ መልሶ የመትከል ሥራ መጀመሩን የሰሜን ምዕራብ ሪጅን አስታወቀ፡፡

በሪጅኑ የማስተላለፊያ መስመሮች ጥገና ሥራ አስኪያጅ አቶ በላይነህ ልጅዓለም እንዳስታወቁት የወደቁትን የኃይል ተሸካሚ የብረት ምሰሶዎች በአፋጣኝ መልሶ በመትከል በአካባቢው አስተማማኝ የኤሌክትሪክ አቅርቦት እንዲኖር ጥረት እየተደረገ ይገኛል፡፡

በአሁኑ ወቅት የሁለት የኃይል ተሸካሚ የብረት ምሰሶዎችን መልሶ የመትከል ሥራ መጠናቀቁን ገልፀው የቀሪዎቹን ተከላ ለማከናወን በአካባቢው ያለው ዝናባማ የአየር ሁኔታ እንቅፋት መፍጠሩን ተናግረዋል፡፡



በተጨማሪም ምሰሶዎቹ በአርሶ አደሮች የሰብል ማሳ ላይ በመውደቃቸው እንደተፈለገው ተንቀሳቅሶ ለመስራት አስቸጋሪ በመሆኑና ብረቶቹ በመሰረቃቸው ምክንያት የማሻሻያ (Modification) ሥራዎችን ማከናወን በማስፈለጉ በመልሶ ተከላ ሥራው ላይ መጠነኛ መዘግየት እንዳስከተለ አብራርተዋል።

ይሁን እንጂ ሪጅኑ የኃይል ተሸካሚ የብረት ምሰሶዎችን መልሶ የመተካት ሥራውን በአጭር ጊዜ ውስጥ በማጠናቀቅ የኃይል ማስተላለፊያ መስመሩ ዳግም አገልግሎት እንዲሰጥ ለማድረግ ርብርብ እየተደረገ ነው ብለዋል፡፡

እንደ አቶ በላይነህ ገለፃ የመልሶ ግንባታ ሥራው ሲጠናቀቅ የሸኽዲ ባለ 230 ኪሎ ቮልት የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያ ዳግም አገልግሎት እንዲሰጥ ያስችላል፡፡

ይህም ከዚህ ቀደም በጊዜያዊነት ከሱዳን ኤሌክትሪክ ሲያገኙ ለነበሩት የምዕራብ ጎንደር ከተሞችና አካባቢዎች ዳግም አስተማማኝና ዘላቂ የኃይል አቅርቦት እዲያገኙ እንደሚያስችላቸውም ነው የገለፁት፡፡

💡 “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”

Scroll to Top