የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች እየገነባቸው የሚገኙ የኃይል መሰረተ ልማት ፕሮጀክቶችን አፈፃፀም እየገመገመ ይገኛል።
የፕሮጀክቶቹ አፈፃፀም በተቋሙ የኢንጅነሪንግና ኮንስትራክሽን ቢዝነስ ዘርፍ ምክትል ዋና ሥራ አሥፈፃሚ ኢንጅነር ውድነህ የማነ፣ በጀነሬሽን ቢዝነስ ዘርፍ ምክትል ዋና ሥራ አሥፈጻሚ ኢንጅነር ኤፍሬም ወልደ ኪዳን እና በትራንስሚሽን ቢዝነስ ዘርፍ ተወካይ ሥራ አሥፈጻሚ ኢንጅነር ደስታዓለም ኃይሉ በኩል ቀርቧል።

ኢንጅነር ደስታዓለም እንደገለፁት በአሁኑ ወቅት የተለያዩ የኪሎ ቮልት መጠን ያላቸው 29 የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያ እና ማስተላለፊያ መስመሮች በተለያዩ የግንባታ ምዕራፎች ላይ ይገኛሉ።
ከእነዚህ ውስጥ ዘጠኙ በጥሩ አፈፃፀም ላይ የሚገኙና በተቀመጠላቸው የጊዜ ገደብ ይጠናቀቃሉ ተብለው የሚጠበቁ መሆናቸውን አብራርተዋል።
ሌሎቹ ፕሮጀክቶች ግን በነዳጅ እጥረት፣ በፀጥታ ችግር፣ በሥራ ተቋራጮች አቅም ማነስ፣ በወሰን ማስከበርና በካሳ ክፍያ መጓተት እንዲሁም በስርቆትና በክትትልና ድጋፍ ማነስ ምክንያት ከተቀመጠላቸው የጊዜ ሰሌዳ ወደ ኋላ የቀሩ መሆናቸውን አብራርተዋል።
በተጨማሪም በዓለም ባንክ እና በአፍሪካ ልማት ባንክ የፋይናንስ ማፅደቅ ሂደቶች በታሰበው ዕቅድ መሠረት ባለመከናወናቸው ምክንያት በፕራይም ፕሮጀክቶች ላይ ከፍተኛ መዘግየት አጋጥሟል።
በሌላ በኩል ኢንጅነር ኤፍሬም ወልደ ኪዳን እንደተናገሩት የኮይሻ የኃይል ማመንጫ ግድብ ግንባታን ጨምሮ ዘርፉ አምስት ፕሮጀክቶችን እየተከታተለ ይገኛል። በእነዚህ ፕሮጀክቶች ላይ ከግብዓት አቅርቦት እና ከዕቃዎች መጓጓዣ ጋር ተያይዘው የሚስተዋሉ ችግሮች ልዩ ትኩረት የሚሹ መሆናቸውን ጠቁመዋል።

በተቋሙ የኮንስትራክሽን ማኔጅመንት የሚሰሩ ፕሮጀክቶችን አፈፃፀም ያቀረቡት ኢንጅነር ውድነህ የማነ በበኩላቸው በአሁኑ ወቅት ከ15 በላይ የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያና ማስተላለፊያ መስመሮች በተለያዩ የግንባታ ሂደት ላይ እንደሚገኙ አንስተዋል።

በአዲሱ አዋጅ መሠረት የወሰን ማስከበርና የካሳ ክፍያ ጉዳዮች ለክልሎች የተሰጠ ኃላፊነት ቢሆንም አዋጁ በተግባር ላይ አለመዋሉ በፕሮጀክቶች አፈጻጸም ላይ እንቅፋት እየፈጠረ መሆኑን ገልፀዋል።
ባለፈው አንድ ዓመት በኮንስትራክሽን ማኔጅመንት የተከናወኑ ፕሮጀክቶች አፈፃፀም ግምገማ የተጠናቀቀ ሲሆን በቅርቡ ለሚመለከታቸው አካላት እንደሚቀርብና ይህም የነበሩ ችግሮችን በመቅረፍ የተሻለ አፈፃፀም በቀጣይ ለማስመዝገብ ጉልህ ሚና እንደሚጫወት አብራርተዋል።

የፕሮጀክቶቹን አፈፃፀም ለማሻሻል የተቋሙ ከፍተኛ አመራር አስቸኳይ የእርምት እርምጃዎችን መውሰድና የተለየ ድጋፍ ሊያደርግ እንደሚገባ ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚዎቹ ያሳሰቡ ሲሆን በአሁኑ ወቅት በቀረቡ የአፈፃፀም ሪፖርቶች ላይ በተሳታፊዎች ውይይት እየተደረገ ይገኛል።







