የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል በሚያከናውናቸው የኃይል መሰረተ ልማት ፕሮጀክቶች አስተዳደርና በሌሎች የአቅም ግንባታ ጉዳዮች ዙሪያ ከተቋሙ ጋር ተባብረው ለመሥራት ዝግጁ መሆናቸውን የቀድሞው የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አሥፈፃሚ ገለፁ፡፡
የቀድሞው ዋና ሥራ አሥፈፃሚ ምህረት ደበበ (ዶ/ር) እንደገለጹት ተቋሙ የኃይል ተደራሽነትን በማረጋገጥ የአፍሪካ የታዳሽ ኃይል ማዕከል ለመሆን በመላ ሀገሪቱ በርካታ የኃይል መሰረተ ልማት ሥራዎችን እያከናወነ ይገኛል፡፡
እነዚህ የመሰረተ ልማት ሥራዎች ዘመኑን የሚመጥኑና ነገን ታሳቢ ያደረጉ እንዲሆኑ የባለሙያዎችን አቅም መገንባት ወሳኝ መሆኑን ያነሱት ዶ/ር ምህረት እርሳቸውም በፕሮጀክት አመራርና አስተዳደር እንዲሁም በተቋማዊ አቅም ግንባታ ዙሪያ ሥልጠናዎችን ለመስጠትና ያላቸውን የካበተ ልምድ ለማካፈል ዝግጁ መሆናቸውን ገልፀዋል፡፡
የተቋሙ ዋና ሥራ አሥፈፃሚ ኢንጂነር አሸብር ባልቻ በበኩላቸው ተቋሙ የአፍሪካ የይቻላል መንፈስ ማሳያ የሆነውን ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ጨምሮ በርካታ ትልልቅ የኃይል መሰረተ ልማት ፕሮጀክቶችን በብቃት ገንብቶ ወደ ኦፕሬሽን ማስገባቱን ተናግረዋል፡፡
በዚህ ሂደት የነበሩ ጠንካራ ጎኖችንና ልምዶችን በቀጣይ በሚገነቡ ፕሮጀክቶች ላይ በመጠቀም የተቋሙን ውጤታማነት ለማረጋገጥ በርካታ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑንም አብራርተዋል፡፡
ተቋሙ በፕሮጀክት አፈፃፀምና አስተዳደር እንዲሁም በኦፕሬሽን ሥራዎች ላይ እያጋጠሙ ያሉ ችግሮችንና ተግዳሮቶችን ለመፍታት በአቅም ግንባታ ላይ ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ እንደሚገኝ ኢንጂነር አሸብር ገልፀዋል።
የቀድሞ የተቋሙ አመራሮችንና ባለሙያዎችን ልምድና እውቀት መጠቀም አስፈላጊ ነው። ለዚህ ተግባር ተቋሙ ተገቢውን ድጋፍና ምቹ መደላድል በመፍጠር አብሮ ለመሥራት ዝግጁ መሆኑን ዋና ሥራ አሥፈፃሚው አረጋግጠዋል፡፡
💡 “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”
