የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል በእንጅባራና አካባቢው የሚስተዋለውን የኃይል አቅርቦት ችግር በዘላቂነት ለመፍታት ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሰራ የተቋሙ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ኢንጂነር አሸብር ባልቻ ገለፁ፡፡
ዋና ሥራ አስፈፃሚው የእንጅባራና የዳንግላ ከተሞችን ወክለው ከመጡ የሕዝብ እንደራሴዎች፣ ከንግድ ማኅበራት ምክር ቤትና ከተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ተወካዮች ጋር በአካባቢው የኃይል አቅርቦት ችግሮችና መፍትሔዎቻቸው ዙሪያ ተወያይተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ሥራ አስፈፃሚ
በውይይቱ ወቅት የአካባቢው ተወካዮች እንደገለጹት የኃይል አቅርቦት ችግሩ በየጊዜው እየተባባሰ በመምጣቱ ምክንያት ኅብረተሰቡ ለተለያዩ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውሶች እየተዳረገ ይገኛል።
ይህም በአካባቢው በተለያዩ የኢንቨስትመንት ዘርፎች ላይ በተሰማሩ ባለሀብቶችና በነዋሪው የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እያሳደረ መሆኑን ተወካዮቹ አስገንዝበዋል።
የኃይል አቅርቦት ጥያቄ ይዘው ወደ ተቋሙ የሄዱ የእንጅባራ ማኅበረሰብ ተወካዮች በዋና ሥራ አስፈፃሚው በኩል ምላሽ ተከልክለዋል ተብሎ በአንዳንድ የማኅበራዊ ሚዲያ ገጾች ላይ ከዚህ በፊት የተሰራጨው መረጃ የአካባቢው የኃይል አቅርቦት ችግር እንዳይፈታ በሚፈልጉ አካላት የተቀናበረ መሆኑን አስታውቀዋል።




የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል በመላ ሀገሪቱ በርካታ የኃይል መሰረተ ልማት ሥራዎችን እያከናወነ መሆኑን ጠቅሰው ተቋሙ ለእንጅባራና ዳንግላ አካባቢዎች ልዩ ትኩረት በመስጠት ለችግሩ መፍትሔ እንዲሰጥም ጠይቀዋል፡፡
በተቋሙ የትራንስሚሽን ቢዝነስ ዘርፍ ተወካይ ምክትል ዋና ሥራ አስፈፃሚ ኢንጂነር ደስታለም ኃይሉ እንደገለጹት በአካባቢው ያለውን የኃይል አቅርቦት ችግር በዘላቂነት ለመቅረፍ የእንጅባራ የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያ በዓለም ባንክ የፋይናንስ አቅርቦት በፕራይም-1 ፕሮጀክት እንዲካተት ተደርጓል።

የትራንስሚሽን ቢዝነስ ዘርፍ ተወካይ ምክትል ዋና ሥራ አስፈፃሚ
ፕሮጀክቱን ተግባራዊ ለማድረግ እስካሁን የቦታ መረጣ እንዲሁም የአካባቢያዊና ማኅበራዊ ተፅዕኖ ግምገማ ጥናቶች መካሄዳቸውን የጠቀሱት ምክትል ዋና ሥራ አስፈፃሚው የሥራ ተቋራጭ ግዥ የጨረታ ሰነድ ተዘጋጅቶ ለዓለም ባንክ መላኩንም አስታውቀዋል።
ለኃይል ማከፋፈያ ጣቢያውና ለማስተላለፊያ መስመር ፕሮጀክቱ ትግበራ 3 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር በጀት መያዙን ገልፀው ግንባታውን ለማጠናቀቅ የ18 ወራት ጊዜ እንደሚወስድም አብራርተዋል።
በከተማዋ የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያ ለመገንባት ከ6 ዓመታት በፊት ታስቦ የነበረ ቢሆንም በግዥ ሂደት መጓተትና በተለያዩ ምክንያቶች ሳቢያ በወቅቱ ወደ ግንባታ አለመገባቱን አስታውሰዋል።
የተቋሙ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ሙላት ገዛኸኝ በበኩላቸው ተቋሙ በአማራ ክልል የኃይል ተደራሽነትን ለማስፋት በትኩረት እየሠራ መሆኑን ገልጸው በእንጅባራ ከተማና አካባቢው የሚስተዋለውን የኤሌክትሪክ አቅርቦት ችግር ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ጋር በጋራ በመፍታት የኅብረተሰቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እንደሚሠራ አስታውቀዋል።

ዋና ሥራ አስፈፃሚ ጽ/ቤት ኃላፊ
የተቋሙ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ኢንጂነር አሸብር ባልቻ በውይይቱ ማጠቃለያ ላይ እንደገለጹት በአገር አቀፍ ደረጃ አሁንም ድረስ 50 በመቶ የሚሆነው የኅብረተሰብ ክፍል የኤሌክትሪክ ኃይል ተጠቃሚ አይደለም።
ስለሆነም ተቋሙ በመላው ሀገሪቱ የኃይል ተደራሽነትን ለማስፋት በትኩረት እየሠራ ቢሆንም ፕሮጀክቶቹ ከፍተኛ የፋይናንስ አቅርቦት የሚጠይቁና አብዛኞቹ ዕቃዎች ከውጭ አገር የሚገቡ በመሆናቸው አገልግሎቱን በሚፈለገው ፍጥነትና መጠን ተደራሽ ማድረግ አለመቻሉን አስረድተዋል።
በክልሉ ያለውን የኃይል ተደራሽነት ለማስፋት የእንጅባራ የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያ እና ማስተላለፊያ መስመርን ጨምሮ በዓለም ባንክ የፋይናንስ አቅርቦት በፕራይም-1 ስር የሚከናወኑ አምስት ተመሳሳይ ፕሮጀክቶች መለየታቸውን ዋና ሥራ አስፈፃሚው ጠቁመዋል።
ተቋሙ የእንጅባራና አካባቢውን የኃይል አቅርቦት ችግር በዘላቂነት ለመቅረፍ በትኩረት እየሠራ እንደሚገኝም ነው ዋና ሥራ አስፈፃሚው የገለፁት፡፡
ምንም እንኳን ከተማዋና አካባቢው የኃይል አቅርቦት እያገኙበት ያለው የዳንግላ ባለ 66 ኪሎ ቮልት የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያና ማሰራጫ መስመሮች በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የሚተዳደሩ ቢሆኑም ችግሩን በጊዜያዊነት ለመፍታት ተቋሙ ከአገልግሎት መስሪያ ቤቱ ጋር በቅንጅት እንደሚሠራ አስታውቀዋል።

ችግሩን በዘላቂነት ለመቅረፍ የሚከናወነውን ፕሮጀክት ስኬታማ ለማድረግ የሁሉም ባለድርሻ አካላት ድጋፍና ክትትል እንደሚያስፈልግም ዋና ሥራ አስፈፃሚው አሳስበዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ‘ዘ-ሀበሻ’ የተሰኘው ሚዲያ ሰኔ 1 ቀን 2018 ዓ.ም በማኅበራዊ ትስስር ገጹ ያሰራጨውና “የእንጅባራ ከተማ የማኅበረሰብ ተወካዮችና የሀገር ሽማግሌዎች በዋና ሥራ አስፈፃሚው ምላሽ ተከልክለዋል” የሚለው ዘገባ ሀሰተኛ መሆኑን ተቋሙ አስታውቋል።
እንዲህ ዓይነቱ የተዛባ መረጃ የተቋሙን መልካም ስምና ገጽታ ለማጉደፍ የተፈጠረ እንጂ በተጨባጭ መሬት ላይ ያለውን እውነታ የሚያሳይ አይደለም። በመሆኑም ተቋሙ ለማኅበረሰብ ተወካዮችና ለባለድርሻ አካላት ምንጊዜም በሩ ክፍት መሆኑን ያረጋግጣል፡፡
