ማከፋፊያ ጣቢያው በአካባቢው መኖሩ የከተማዋን ኢኮኖሚ አነቃቅቷል

ማከፋፊያ ጣቢያው በአካባቢው መኖሩ የከተማዋን ኢኮኖሚ አነቃቅቷል

የቦንጋ ማከፋፈያ ጣቢያ የከተማዋን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ማነቃቃቱን የቦንጋ ከተማ ከንቲባ ተክለአብ ቡሎ (ዶ/ር) ተናገሩ፡፡

በከተማዋ የሚገኘው የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያ ለአካባቢው የኢኮኖሚ መነቃቃት ለኢንቨስትመንት መስፋፋትና ለአገልግሎት ሰጪ ተቋማት መበራከት ከፍተኛ ሚና መጫወቱንም ከንቲባው ገልፀዋል።

በከተማው አስተማማኝ የኃይል አቅርቦት በመኖሩ በተለያዩ ዘርፎች ኢንቨስትመንቶች እንዲስፋፉ ትልቅ መነቃቃት የፈጠረ መሆኑን የገለፁት ከንቲባው በተለይ ደረጃቸውን የጠበቁ ሆቴሎችና የተለያዩ ማህበራዊ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት በየአቅጣጫው እንዲበራከቱ እና የማህበራዊ ግንኙነቶች እንዲጠናከሩ ማድረጉንም ተክለአብ አድርጓል (ዶ/ር) አስረድተዋል።

ከ10 ዓመታት በፊት በከተማዋ ታሪክ የነበረውን የግል የጤና ተቋማት እጥረት በመጥቀስ በአሁኑ ወቅት የኃይል አቅርቦቱ አስተማማኝ በመሆኑ በርካታ የግል ጤና ጣቢያዎችና ሆስፒታሎች በስፋት እየተገነቡ እንደሚገኙ አስታውቀዋል።

ወደ ከተማዋ የሚመጣ ማንኛውም ባለሀብት በቅድሚያ የሚያነሳው የኃይል አቅርቦት ጥያቄ መሆኑን ያነሱት ከንቲባው የማከፋፈያ ጣቢያው መኖር ኢንቨስተሮች ያለምንም ማቅማማት ወደ ሥራ እንዲገቡ ትልቅ መተማመን መፍጠሩን አብራርተዋል።

በሚቀጥሉት ሁለት ዓመታት ባለው ጊዜ ውስጥ የሚጠናቀቁ ፕሮጀክቶች ከተማዋን እድገት አንደሚያፋጥነው እና ከተማዋን ወደ ተሻለ ከፍታ ያደርሰዋል ያሉት ከንቲባው ለዚህም የኃይል አቅርቦቱ ድርሻ የጎላ እንደሆነ ገልፀዋል፡፡ ይህም የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት ለማሳደግ እና ወጣቶችን በማደራጀት የሥራ ዕድል እየተፈጠረ ይገኛል ብለዋል።

ከተማዋን የማዘመን እና የነዋሪውን ሕይወት ለማሻሻል በሚደረገው ጥረት የማከፋፈያ ጣቢያው ድርሻ ከፍተኛ መሆኑን የጠቀሱት ከንቲባ ተክለአብ (ዶ/ር) በከተማዋና በአካባቢው የኃይል መሰረተ ልማት ስርቆት እንዳይፈጸም ጥብቅ የቁጥጥርና የሕግ ተጠያቂነት አሰራር ተዘርግቶ ተግባራዊ እየተደረገ መሆኑንም አረጋግጠዋል።

Scroll to Top