ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያ ፕሮጀክቱን ጎበኙ

ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያ ፕሮጀክቱን ጎበኙ

ከፍተኛ የፌዴራልና የክልል የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ለገዳ ልዩ የኢኮኖሚ ዞን የኤሌክትሪክ ኃይል ለማቅረብ እየተገነባ የሚገኘውን ባለ 230 ኪሎ ቮልት የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያ ፕሮጀክት ጎበኙ።

በጉብኝቱ ላይ የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳ፣ በሚኒስትር ማዕረግ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የማክሮ ኢኮኖሚ አማካሪና የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የሥራ አመራር ቦርድ ምክትል ሰብሳቢ አምባሳደር ግርማ ብሩ፣ የብሔራዊ ባንክ ገዥ ኢዮብ ተካልኝ (ዶ/ር)ን ጨምሮ ሌሎችም የፌዴራልና የክልል ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ተሳትፈዋል።

በጉብኝቱ ወቅት ለከፍተኛ የሥራ ኃለፊዎቹ ገለፃ ያደረጉት በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የኢንጅነሪንግና ኮንስትራክሽን ቢዝነስ ዘርፍ ምክትል ዋና ሥራ አስፈፃሚ ኢንጂነር ውድነህ የማነ እንደተናገሩት የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያው ግንባታ የመጨረሻው ምዕራፍ ላይ ደርሷል፡፡

ፕሮጀክቱ በሚቀጥሉት ሁለት ሳምንታት ውስጥ ሙሉ በሙሉ አገልግሎት መስጠት ሲጀምር በገዳ ልዩ የኢኮኖሚ ዞን ውስጥ ለሚገኙ ኢንዱስትሪዎች እስከ 200 ሜጋ ዋት ኃይል የማቅረብ አቅም እንደሚኖረው ገልፀዋል፡፡

የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያው የኢንዱስትሪ ዘርፍን ማዕከል አድርጎ መገንባቱን የጠቀሱት ምክትል ዋና ሥራ አስፈፃሚው በዚህም ጣቢያው የኃይል መቋረጥ እንዳያጋጥም የሚያስችል ዘመናዊ ሥርዓት የተዘረጋለት መሆኑን አንስተዋል፡፡

የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያው ከሚኖሩት አራት ባለ 63 ሜጋ ቮልት አምፒር ትራንስፎርመሮች መካከል 50 ሜጋ ዋት ኃይል የመጫን አቅም ያለው አንዱ ትራንስፎርመር በተንቀሳቃሽ ስዊችጊር አማካኝነት ለአንድ ኢንዱስትሪ ኤሌክትሪክ ማቅረብ መጀመሩን ጠቅሰዋል፡፡

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ከዕቃ አቅርቦትና ማጓጓዝ ውጭ ያሉትን እንደ ዲዛይን፣ ግንባታ፣ እንዲሁም የፍተሻና ሙከራ ሥራዎችን ሙሉ በሙሉ በራሱ አቅም ማከናወኑን አብራርተዋል።

የኃይል ማከፋፈያው የገዳ ልዩ ኢኮኖሚ ዞን ለሚፈልገው አገልግሎት ኃይል የሚያቀርቡ 14 ባለ 33 ኪሎ ቮልት ወጪ መስመሮች እንዲኖሩት ተደርጎ እየተገነባ የሚገኝ ጣቢያ ነው፡፡

ጣቢያው ከቆቃ እና ቢሾፍቱ የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያዎች ኤሌክትሪክ የሚያገኝባቸው ሁለት ገቢ መስመሮች እንዳሉት የጠቆሙት ኢንጂነር ውድነህ ከገዳ ልዩ የኢኮኖሚ ዞን ባለሥልጣን ጋር በመተባበር ስድስት የኃይል ማሰራጫ መስመሮች ለአገልግሎት ዝግጁ መደረጋቸውን ገልፀዋል፡፡

የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያው ቀጣይነት ላለው የኢንዱስትሪ ዕድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዲያበረክት ታስቦ ሰፊ የማስፋፊያ ቦታ ተይዞለት የተገነባ መሆኑንም ነው ምክትል ዋና ሥራ አስፈፃሚው ጨምረው ያብራሩት፡፡

💡 “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”

Scroll to Top