በኢነርጂው ዘርፍ ብቁ ባለሙያዎችን ለማፍራት ያለመ የአቅም ግንባታ ስልጠና በዋናው መሥሪያ ቤት መሰጠት መጀመሩን በተቋሙ የኃይል ማመንጫ ጣቢያዎች ማስተባበሪያ አንድ ዳይሬክተር አቶ አብዱ ይማም ገለፁ።
ስልጠናው ከኢንጂነሪንግና ኮንስትራክሽን ዘርፍ እንዲሁም ከጀነሬሽን ኦፕሬሽን ለተውጣጡ የስራ ኃላፊዎች እና ባለሙያዎች የተዘጋጀ መሆኑን የገለፁት ዳይሬክተሩ ስልጠናው በሁለት ዙር የሚሰጥ ነው።


በአሁኑ ወቅትም በዋናው መሥሪያ ቤት ግቢ እየተካሄደ በሚገኘው በመጀመሪያው ዙር 80 የሚሆኑ የስራ ኃላፊዎችና ባለሙያዎች በመሳተፍ ላይ ይገኛሉ።
የመጀመሪያው ዙር ስልጠና በዋናነት በሜካኒካል ስራዎች እና በግድብ ደህንነት ዙሪያ ላይ ትኩረቱን ያደረገ ሲሆን ቀጣዩ የሁለተኛ ዙር ስልጠና ደግሞ በዲዛይንና በኤሌክትሪካል አውቶሜሽን ቴክኖሎጂዎች ላይ እንደሚያተኩር ዳይሬክተሩ ተናግረዋል።



ይህንን ስልጠና በዘርፉ በዓለም አቀፍ ደረጃ ግንባር ቀደም ከሆነው የጀርመኑ ቮይት ሀይድሮ (Voith Hydro) ኩባንያ በመጡ ከፍተኛ ባለሙያዎች እየተሰጠ እንደሚገኝም ጠቁመዋል።
ለአንድ ወር በሚቆየው በዚህ ስልጠና ላይ ጥቅም ላይ የዋሉ የዘመኑ ቴክኖሎጂዎችን ያካተተ መሆኑን የጠቆሙት አቶ አብዱ ስልጠናው ሲጠናቀቅ በጀነሬሽን ኦፕሬሽን እና በኢንጂነሪንግ ዘርፍ የበቁ ባለሙያዎች እንደሚፈጠር ሙሉ እምነት እንዳላቸው ገልፀዋል።
ይህም ተቋሙ የኃይል ማመንጫዎችን በራስ አቅም ለመጠገን ለማስተዳደርና ዘመናዊ ለማድረግ ለሚያደርገው ጉዞ ትልቅ አቅም እንደሚሆን እምነታቸውን ገልፀዋል።
ተቋሙ የተጣለበትን አገራዊ ዋና ተልዕኮ በላቀ ብቃት መፈፀም የሚያስችሉ መሰል የክህሎት ማሳደጊያ እና የአቅም ግንባታ ሥልጠናዎችን ለስራ ኃላፊዎች እና ለባለሙያዎች ወደ ፊትም በተከታታይነት ለመስጠት መታቀዱን ዳይሬክተሩ ጠቁመዋል።


