በተቋሙ ቀጣይነት ያለው ውጤት ለማምጣት ደንበኞችን ማዕከል አድርጎ መሥራት ይገባል

በተቋሙ ቀጣይነት ያለው ውጤት ለማምጣት ደንበኞችን ማዕከል አድርጎ መሥራት ይገባል


በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ቀጣይነት ያለው ውጤት ለማምጣት ደንበኞችን፣ ባለድርሻ አካላትን እና የተለያዩ የአሰራር ሥርዓቶችን ማዕከል ባደረገ መልኩ ሥራዎችን ማከናወን እንደሚገባ በተቋሙ የትራንስሚሽን ቢዝነስ የሰው ኃይልና ንብረት አስተዳደር ዳይሬክተር አሳሰቡ።

ዳይሬክተሩ አቶ ተማም አፍደል ለተቋሙ የሦስተኛ ዙር ሰልጣኖች “በሠራተኞች ተግባርና ኃላፊነት” ዙሪያ ስልጠና በሰጡበት ወቅት እንደተናገሩት ሠራተኛው የተቋሙ ርዕይ፣ ተልዕኮ፣ እሴቶች እና ዓላማዎች ዋና ባለቤት በመሆን ተቋማዊ ዕድገትን የማረጋገጥ እና የሕዝቡን ፍላጎት የማሟላት ኃላፊነት አለበት።

ስለሆነም ተቋሙ የያዛቸውን ዕቅዶች ለማሳካት ሁሉም ሠራተኛ ሚናውንና ኃላፊነቱን በግልፅ ተገንዝቦ መስራት እንደሚኖርበት አንስተዋል።

የተቋሙን ጥቅም ለማስጠበቅ ሠራተኛው መረጃዎችን መልካም ስምና ዝናን ባረጋገጠ እና ተጠያቂነትን ባሰፈነ መልኩ በባለቤትነት ስሜት መጠቀም እንደሚጠበቅበትም አቶ ተማም ጠቁመዋል።

የሠራተኛውን ጥቅማጥቅም ለማስከበር የተቋሙን ዕድገት ማረጋገጥ ያስፈልጋል ያሉት ዳይሬክተሩ ለዚህም ሠራተኛው ለጥራት ትኩረት በመስጠት፣ የሥራ ላይ ደህንነትን በማስጠበቅ እና ለመማር ዝግጁ በመሆን የዕለት ተዕለት ተግባሩን በቁርጠኝነት መስራት እንደሚኖርበት አስገንዝበዋል።

ተቋሙ ረጅም ዓመት ያስቆጠረና በሂደት ዕድገት እያስመዘገበ እንደሆነ በመግለፅ እድገቱን ለማስቀጠልም ሥራዎቹን የደንበኞችን እርካታ በሚያረጋግጥ እና የተለያዩ የአሰራር ሥርዓቶችን ማዕከል ባደረገ መልኩ ማከናወን እንዲሁም ሁሉንም ተቋማዊ ሀብቶች በአግባቡ መጠቀም እንደሚያስፈልግ አቶ ተማም አብራርተዋል።

ተቋሙን በቀጣይነት ለማሻሻልና ጠንካራ ተቋማዊ ባህል ለመገንባት የእርስ በዕርስ መማማር ባህልን በማጎልበት ብቃትን ማሳደግ፣ መረጃዎችን በማደራጀት ለቀጣዩ ትውልድ ማሸጋገር እና የተቋሙን እሴቶች ከማወቅ ባለፈ በተግባር መግለፅ እንደሚገባ አቶ ተማም አፅንኦት ሰጥተዋል።

በተጨማሪም ለለውጥ ዝግጁ መሆንና ለውጡን መረዳት፣ የዲጂታል ሥርዓትን ማስፋፋት፣ የፈጠራ ባህልን ማጎልበት፣ የእርስ በእርስ ግንኙነትን ማጠናከር፣ ርዕይን የጋራ ማድረግ እና የተጠያቂነትና ግልፅነት ሥርዓትን ማስፈን እንደሚያስፈልግ ነው የተናገሩት።

ሠራተኛው ያሉ ክፍተቶችን በጋራ በመፍታትና የቡድን ሥራን በማጠናከር ተቋሙን ወደ ተሻለ ደረጃ ለማድረስና ጠንካራ ተቋማዊ ባህል ለመገንባት በሚከናወነው ሥራ ኃላፊነቱን በአግባቡ መወጣት እንዳለበትም አሳስበዋል።

Scroll to Top